ኢትዮጵያ በተፈጥሮ ፀጋዎቿ የበለጸገች፣ የማዕድን፣ የኃይል፣ የለምለም መሬት እና የውኃ ሀብት ባለቤት ብትሆንም ይህ ሁሉ እምቅ አቅም ለበርካታ ዓመታት ተቆልፎበት፣ የሀገራችን ስም ከድህነት ጋር ተያይዞ ቆይቷል።
"በወርቅ ድስት ላይ የተቀመጠ ድሃ" የሚለው አባባልም የዚሁ እውነታ ማሳያ ሆኖ ቆይቷል።
አሁን ግን ይህ ታሪክ እየተቀየረ ይገኛል፤ ኢትዮጵያ በመደመር ዕሳቤ መሪነት ከመሬት በላይ እና ከመሬት በታች የተኙ ሀብቶቿን ቀስቅሳ ወደ ታላላቅ ሜጋ ፕሮጀክቶች በመቀየር ለሕዝቧ ጥቅም ለማዋል አዲስ መንገድ ጀምራለች።
የመደመር ዕሳቤ ዋና ሕልም ያለፈውን ሀገራዊ አቅም እና ያልተጠቀሙበትን የተፈጥሮ ፀጋ ከአዲሱ ዘመን ቴክኖሎጂ እና እውቀት ጋር በማጣመር የኢኮኖሚ ነፃነትን ማረጋገጥ ነው።
በዚህ ዕሳቤ የተቀረጹት ሜጋ ፕሮጀክቶችም ሀገራችን ለዘመናት የነበራትን የውጭ ጥገኝነት የመስበር አቅም ያላቸው ናቸው።
ከእነዚህም መካከል ግብርናውን ከዝናብ ጥገኝነት በማላቀቅ በበጋ ስንዴ ልማት የታየው ስኬት ተጠቀሽ ነው፤ ቀደም ሲል ከውጭ ይገባ የነበረውን ስንዴ በሀገር ውስጥ ምርት ከመተካት አልፋ ለውጭ ገበያ ማቅረብ የሚችል ሜጋ የአግሮ-ኢንዱስትሪ አቅም ተገንብቷል።
በተጨማሪም በመሬት ሥር የተሸሸጉ የማዕድን እና የኃይል ሀብቶችን አውጥቶ የመጠቀም ሥራው በሜጋ ፕሮጀክቶች ደረጃ ትልቅ ትኩረት ተሰጥቶታል። በኦጋዴን እና በሌሎች አካባቢዎች የሚገኙ ተፈጥሮ ጋዝ እና የነዳጅ ሀብቶችን አልምቶ ወደ ጥቅም ለመቀየር የተጀመሩት ታላላቅ ፕሮጀክቶች ሀገራችን የኢንዱስትሪ እና የኃይል አቅሟን የሚያሳድጉ ናቸው።
ከዚሁ ጎን ለጎንም የወርቅ፣ የከሰል ድንጋይ እና የፖታሽ ማዕድናትን በዘመናዊ የኢንዱስትሪ ማቀነባበሪያዎች የመቅረጽ ሥራ ከውጭ የሚገቡ ምርቶችን በሀገር ውስጥ የመተካት እና የውጭ ምንዛሬ የማስገኘት አቅማቸውን በከፍተኛ ሁኔታ አሳድጎታል።
ከማዕድን እና ግብርና ባሻገር ሀገራዊ ትሥሥርን እና የንግድ ፍሰትን የሚያፋጥኑ የመሠረተ ልማት ሜጋ ፕሮጀክቶችም የመደመር ዕሳቤ አካል ናቸው።
የኢንዱስትሪ ፓርኮች መስፋፋት፣ የሎጂስቲክስ እና የትራንስፖርት መዋቅሮች ማዘመን፣ እንዲሁም የኃይል ማመንጫ እና ማሰራጫ አውታሮች ዝርጋታ የተፈጥሮ ሀብቱ ቀጥታ ወደ ሀብት እንዲቀየር መንገድ ከፍተዋል።
እነዚህ ሜጋ ፕሮጀክቶች ሀገራችን ያለችበትን የጂኦ-ፖለቲካዊ እና የተፈጥሮ ፀጋ አቀማመጥ ተጠቅማ ቀጣናዊ የንግድ ማዕከል እንድትሆን መሠረት እየጣሉ ይገኛሉ። ኢትዮጵያ ከተፈጥሮ ሀብት ባለቤትነት ወደ ሀብት ተጠቃሚነት የምታደርገው ሽግግር አዲስ ተስፋን ፈጥሯል።
በመደመር ዕሳቤ የተቀረጹት ሜጋ ፕሮጀክቶች የተፈጥሮ ሀብትን ከአካባቢ ጥበቃ እና ከዘላቂ ልማት ጋር አጣጥሞ በመጠቀም የዜጎችን ሕይወት ለማሻሻል የተወጠኑ ናቸው።
ይህ የልማት አካሄድ በተዋቀረ መንገድ ቀጣይነቱ ከተጠበቀ፣ ኢትዮጵያ የማዕድን፣ የግብርና እና የኃይል ፀጋዎቿን ሙሉ በሙሉ በመጠቀም እውነተኛ የኢኮኖሚ ነፃነቷን የምታረጋግጥበት ጊዜ ሩቅ አይሆንም።
በሔዋን ጌታቸው
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: