የኢትዮጵያ የቴአትር ጥበብ ታሪክ አንድ ምዕተ ዓመት ያስቆጠረ ቢሆንም፣ ከሁለተኛው የጣሊያን ወረራ በኋላ በአዲስ አበባ የዘርፉ መሠረተ ልማት ዕድገት እጅግ አዝጋሚ ሆኖ ቆይቷል።
ዘመኑን የዋጁ የጥበብ ሥራዎች ማሳያ ስፍራዎች ባለመገንባታቸው፣ ዘርፉ እርጅና በተጫናቸው እንደ ሲኒማ አምፒር፣ ሲኒማ ኢትዮጵያ እና አምባሳደር ሲኒማ ባሉ ጥቂት ጥንታዊ የጥበብ ቤቶች ላይ ብቻ ተደግፎ ኖሯል።
ይህ የማሳያ ቦታዎች እጥረት የፈጠራ ሥራዎች በተገቢው መንገድ ወደ ተደራሲያን እንዳይቀርቡ በማድረግ በባለሙያዎች ላይ የሙያ እና የኢኮኖሚ ፈተና ደቅኖ ዘልቋል።
አሁን ላይ ግን አዲስ አበባ ዘመናዊ የጥበብ መሠረተ ልማቶችን በማስፋፋት ረገድ ታሪካዊነቷን በሚመጥን መልኩ ዳግም እየተወለደች ትገኛለች።
ኪነ ጥበብን በጠባብ አዳራሽ ግርግዳዎች ከመገደብ አውጥቶ ከተፈጥሮ ጋር ለማዋሃድ እንደ ወዳጅነት፣ አምባሳደር፣ ኢሬቻ፣ ፒኮክ፣ የኮርያ ዘማቾች እና ሐምሌ 19 ባሉ ፓርኮች ዘመናዊ የሜዳ ላይ (ከቤት ውጭ) አምፊ ቴአትሮች ተገንብተዋል።
እነዚህ ስፍራዎች ለታላላቅ ባህላዊ እና ጥበባዊ ሁነቶች ምቹ መድረክ በመሆን ጥበብን ለሕዝብ ይበልጥ ተደራሽ እያደረጉ ነው።
ከዚህ ጎን ለጎን አዲሱን ትውልድ በኪነ ጥበብ አንፆ ለማሳደግ ታላላቅ ማዕከላት ተገንብተዋል።
ከ1 ሺህ 500 በላይ ሰዎችን የሚያስተናግዱ የቴአትር እና የሲኒማ አዳራሾችን የያዘው የህፃናት እና ወጣቶች ኮምፕሌክስ፤ እንዲሁም በ24 ሺህ ካሬ ሜትር ላይ ያረፈው ባለ 15 ወለሉ አዲስ ሲኒማ ኮምፕሌክስ ለዚህ ማሳያዎች ናቸው።
በታሪካዊቷ ፒያሳ ደረቱን ነፍቶ የቆመው የዓድዋ ድል መታሰቢያ፣ ባለ 2 ሺህ 500 ወንበሩን የፓን አፍሪካኒዝም አዳራሽ እና ታሪካዊ ስያሜ የተሰጣቸው ሲኒማ ቤቶችን በውስጡ በማካተት ከተማዋን ወደ ላቀ የጥበብ ማዕከልነት አሸጋግሯታል።
አዳዲስ የኪነ-ጥበብ ፕሮጀክቶች ቢበራከቱም ነባሮቹም አልተዘነጉም፤ ታሪካዊው አዲስ አበባ ቴአትር እና ባህል አዳራሽ (ማዘጋጃ ቤት) እና የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቴአትር በዘመናዊ የድምጽ እና የብርሃን ቴክኖሎጂዎች በላቀ ደረጃ ታድሰዋል።
በግሉ ዘርፍ እየተገነቡ ያሉ ዘመናዊ የሲኒማ ማዕከላትም የአዲስ አበባ የኪነ ጥበብ ትንሣኤ አካል ሆነዋል።
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ለጥበብ ዕድገት የዘረጋውን ምቹ ምህዳር ይበልጥ ትርጉም እንዲኖረው ያደረገው ደግሞ ለባለሙያዎች የተሰጠው ክብር ነው።
የከተማ አስተዳደሩ በቂርቆስ ክፍለ ከተማ በዘመናዊ መልኩ የተገነቡ የመኖሪያ ቤቶችን ለአንጋፋ አርቲስቶች በስጦታ በማበርከት ታሪካዊ ውለታቸውን መልሷል።
በከተማዋ መልሶ ግንባታ እና የኮሪደር ልማት በሕይወት ላሉ እና ላለፉ አንጋፋ የኪነ ጥበብ ባለሙያዎች መታሰቢያዎች መካተታቸውም የላቀ ትርጉም ያለው ሰው ተኮር ተግባር ነው።
በዘመናዊ መልክ የተገነቡት እነዚህ አዳዲስ እና ነባር የኪነ ጥበብ ማዕከላት ለከያኒያን ሰፊ የፈጠራ ዕድል ከመስጠታቸውም በላይ፣ አዲሱን ትውልድ በኢትዮጵያዊ እሴቶች ኮትኩቶ ለማሳደግ ጉልህ ሚና እየተጫወቱ ይገኛሉ።
በለሚ ታሰደ
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: