የደብረ ማርቆስ ከተማ ከ70 ዓመት በፊት በኢትዮጵያ ካሉ ምርጥ ከተሞች ተወዳድራ አንደኛ የወጣችበትን የታሪክ ክብርና ቁመና እንድትመልስ፣ ሕዝቡ ለሰላም ቅድሚያ ሊሰጥ እንደሚገባ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) አሳሰቡ።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በደብረ ማርቆስ የንጉሥ ተክለ ሃይማኖት አውሮፕላን ማረፊያን በይፋ ሲመርቁ እንዳሉት፣ ከተማዋ በግጥም ጭምር "ቢሻህ በአውሮፕላን፣ ቢሻህ በሎንቺና" እየተባለች የምትወደስ የብልጽግና ተምሳሌት ነበረች።
ዛሬ "ቢሻህ በአውሮፕላን" የሚለው የታሪክ እውነት ቢመለስም፣ "ቢሻህ በሎንቺና" የሚለውን ለመመለስ ግን የሁሉንም ዜጋ ጥረት እንደሚጠይቅ አስገንዝበዋል።
የአካባቢውን ለምለም ተፈጥሮ ያነሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ እንዲህ ያለ የተፈጥሮ ጸጋ ይዞ ተግባብቶና ተዋዶ ከመኖር ይልቅ፣ በዘር፣ በጎጠኝነትና በጽንፈኝነት መከፋፈል ሀገራችንን ከመጉዳት ውጪ ፋይዳ የሌለው መሆኑን ገልጸዋል።
ደብረ ማርቆስ በትናንትናው ታሪኳ ወሎንና ወለጋን በማስተሳሰር የንግድና የዕድገት ድልድይ እንደነበረች ያስታወሱት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ፣ አካባቢው ከተለያዩ ብሔረሰቦች ጋር ተዋህዶ የኖረ ማህበረሰብ በመሆኑ ለሌላው ወገን የአንድነትና የሰላም አርዓያ መሆን እንደሚገባው ተናግረዋል።
ሕዝቡ ከጸጥታ አካላት ጋር በመቀናጀት የአካባቢውን ሰላም በጋራ በመጠበቅ፣ በነፃነት የመንቀሳቀስና የመሥራት መብቱን ማስከበር እንዳለበት ጥሪ አቅርበዋል።
የደረስንበትን የልማት ምዕራፍ ለማስቀጠልና የከተማዋን የቀድሞ ስም ለመመለስ መላው ማኅበረሰብ በተደማመጠ፣ በተከባበረና በተደመረ መንፈስ ለጋራ ብልጽግና እንዲተጋም አደራ ብለዋል።
በሃይማኖት ከበደ
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: