Search

የኢትዮጵያ የአቪዬሽን አብዮት እና የቱሪዝም ትስስር

እሑድ ሐምሌ 05, 2018 52

ኢትዮጵያ በአየር ትራንስፖርት ዘርፍ እያደረገችው ያለው ፈጣን አህጉራዊ እና ዓለም አቀፋዊ ተጽዕኖ፣ ሀገራችን ለመሠረተ ልማት መስፋፋት የሰጠችውን ከፍተኛ ትኩረት በግልጽ የሚያሳይ ነው።

የዚህ ተከታታይ የልማት ጉዞ ማሳያ የሆነውና ዛሬ በይፋ የተመረቀው የደብረ ማርቆስ ንጉሥ ተክለ ሃይማኖት አውሮፕላን ማረፊያ፣ የኢትዮጵያን የአቪዬሽን ኢንዱስትሪ ወደ አዲስ ምዕራፍ ያሸጋገረ ታሪካዊ ክስተት ነው። በዚህም ከተማዋ ለሰላሳ ዓመታት ተቋርጦ የቆየውን የአየር ትራንስፖርት አገልግሎት ዳግም አግኝታለች።

ይሁን እንጂ፣ ይህ ሀገራዊ የአቪዬሽን ስኬት በደብረ ማርቆስ ብቻ የሚያበቃ አይደለም። መንግሥት በራዕይ 2035 ዕቅዱ መሠረት ኢትዮጵያን የአፍሪካ ቀዳሚ የትራንስፖርት እና ሎጂስቲክስ ማዕከል ለማድረግ በትኩረት እየሰራ ይገኛል።

ለዚህም ዋነኛ ማሳያ የሚሆነው፣ በቅርቡ በቢሾፍቱ ከተማ እውን የሚሆነው የሜጋ አውሮፕላን ማረፊያ ፕሮጀክት ነው። ይህ ዓለም አቀፍ ደረጃውን የጠበቀ ግዙፍ ፕሮጀክት ሲጠናቀቅ የሀገራችንን የመንገደኞችና የጭነት ማስተናገድ አቅም በከፍተኛ ደረጃ በማሳደግ፣ የኢትዮጵያን የትራንዚት አቅም ከዓለም ታላላቅ የመጓጓዣ ማዕከላት ጋር ተወዳዳሪ ያደርገዋል። ይህም ኢትዮጵያን ከሌሎች የዓለም ታላላቅ የመጓጓዣ ማዕከላት ተርታ በኩራት ያሰልፋታል።

የእነዚህ ግዙፍ የአየር መሠረተ ልማቶች መስፋፋት ፋይዳ ከትራንስፖርት አገልግሎት ባሻገር እጅግ ሰፊ ሲሆን፣ አንደኛ ሀገራችን ያሏትን እምቅ የቱሪዝም መዳረሻዎች ለዓለም አቀፍ እና ለሀገር ውስጥ ጎብኚዎች በቀላሉ ተደራሽ ያደርጋል። የቱሪስቶች ፍሰት ሲጨምር የአካባቢው የንግድ፣ የኢንቨስትመንትና የእንግዳ ተቀባይነት ዘርፍ በከፍተኛ ሁኔታ ይነቃቃል።

ሁለተኛ፣ ርቀትን በማጥበብ በሀገራችን የተለያዩ አካባቢዎች የሚገኙ ዜጎች በቀላሉ እንዲገናኙ በማድረግ ጠንካራ የሕዝብ ለሕዝብ ትስስርን ይፈጥራል።

ዘመናዊ መሠረተ ልማት የኢኮኖሚ ዕድገት ዋነኛ ሞተር ነው። በአጠቃላይ የደብረ ማርቆስ አውሮፕላን ማረፊያ ዳግም መከፈትም ሆነ የቢሾፍቱ ሜጋ ኤርፖርት ግንባታ ራዕይ፣ ኢትዮጵያ በመሰረተ ልማት ትስስር ወደ ላቀ ደረጃ እየተሸጋገረች መሆኗን የሚያረጋግጡ ህያው ምስክሮች ናቸው።

ፈተናዎችን ወደ ዕድል በመቀየር አዳዲስ የኢኮኖሚ ምዕራፎችን መክፈት መቻሉ፣ ሀገራችንን ተወዳዳሪ የቱሪስት መዳረሻ፣ የንግድ ማዕከል እና የኅብረ ብሔራዊ አንድነት ተምሳሌት እንድትሆን ሰፊ መንገድ ጠርጓል።

ወደፊትም እነዚህ ግዙፍ ፕሮጀክቶች በተያዘላቸው የጊዜ ሰሌዳ ሲጠናቀቁ ሀገራችን በዓለም አቀፍ ደረጃ ያላትን ትልቅ ተወዳዳሪነት በይበልጥ እንደሚያጎላው ጽኑ እምነት በስፋት ተጥሎበታል።

በአዶኒያስ ወ/አረጋይ

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: