ከሳምንታት በፊት በአሜሪካ እና ኢራን መካከል በተደረሰው የተኩስ አቁም ስምምነት ወደ ሰላማዊ አየር የተመለሰው መካከለኛው ምስራቅ በሁለቱ ሀገራት መካከል ዳግም በተቀሰቀሰው ጦርነት ውጥረት ውስጥ ገብቷል።
የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ከኢራን ጋር የተደረሰው የተኩስ አቁም ስምምነት አክትሟል ብለው ከተናገሩ በኋላ፣ የአሜሪካ ጦር በኢራን ላይ በሁለት ዙር በፈጸመው ወታደራዊ ጥቃት ከ90 በላይ ወታደራዊ ኢላማዎች መምታቱን አስታውቋል።
ኢራን በሦስት የንግድ መርከቦች ላይ ጥቃት መፈጸሟ የግጭቱ መነሻ መሆኑን የገለጸችው አሜሪካ፣ በአጸፋዊ ምላሿ 65 የኢራን አብዮታዊ ዘብ ወታደራዊ ጀልባዎችን ማውደሟን ገልጻለች።
በአሜሪካ የቀረበባትን ውንጀላ በሙሉ ውድቅ ያደረገችው ኢራን፣ በባህሬን እና ኩዌት የሚገኙ የአሜሪካ ወታደራዊ ሰፈሮችን በመምታት አጸፋዊ ምላሽ መስጠቷ ተገልጿል።
የኢራን ባለስልጣናት “ይህ ጨዋታ አይደለም፤ ጥቃት ሲሰነዘርብን በዝምታ አንመለከትም” በማለት ተጨማሪ እርምጃዎችን እንደሚወስዱም አስጠንቅቀዋል።
አሜሪካ በባሕር የንግድ መስመሮችን እና የአጋሮቿን ደኅንነት ለማስጠበቅ እርምጃ እንደወሰደች ስትገልጽ፣ ኢራን በበኩሏ በቀጣናው ውስጥ በራሷ ላይ የሚፈጸሙ ወታደራዊ ጫናዎችን ለመመከት እንደምትንቀሳቀስ ማሳወቋን አልአረቢያ ዘግቧል።
የጦርነቱ ተፅዕኖ ከወታደራዊ ጉዳይ አልፎ በዓለም ኢኮኖሚ ላይም መታየት ጀምሯል።
በተለይ በዓለም የነዳጅ ንግድ የ20 በመቶ መተላለፊያ የሆነው የሆርሙዝ ወሽመጥ በውጥረት ውስጥ መግባቱ የዓለም የነዳጅ ዋጋ በዚህ ሳምንት ብቻ 5 በመቶ እንዲጨምር አድርጓል።
እንደ ባለሙያዎቹ አስተያየት ግጭቱ ከተባባሰ በኃይል ገበያዎች፣ በዓለም ንግድ እና በክልላዊ ደኅንነት ላይ የበለጠ ተፅዕኖ ሊያሳድር እንደሚችል እያስጠነቀቁ ይገኛሉ።
ምንም እንኳን በአሜሪካ እና ኢራን መካከል ለሁለተኛ ቀን ጥቃቱ ቢቀጥልም ኢራን በጦርነቱ ጅማሮ ላይ የተገደሉት የቀድሞው ጠቅላይ መሪ የአያቶላህ አሊ ኻሜኒ የቀብር ሥነ ሥርዓት በዛሬው ዕለት ተፈጽሟል።
በሀብተሚካኤል ክፍሉ