Search

ከታሪክ ማህደር ወደ ዘመናዊ ብልጽግና፤ የደብረ ማርቆስ አዲስ አድማስ እና የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ጥሪ

እሑድ ሐምሌ 05, 2018 54

ባለፈው ዘመን በግጥም እና በዜማ "አትመጣም ወይ ማርቆስ ከተድላው ከተማ፣ ቢሻህ በአውሮፕላን…." ተብሎ ሲወደስ የኖረው የደብረ ማርቆስ ከተማ ሰማይ፣ ዛሬ በድጋሚ የአውሮፕላን ድምጽ አስተጋብቷል።

የሰባ ዓመታት የታሪክ አሻራ የነበረው እና ለሦስት አስርት ዓመታት ተቀዛቅዞ የቆየው የደብረ ማርቆስ ንጉሥ ተክለ ሃይማኖት አውሮፕላን ማረፊያ፣ በዘመናዊ መልክ ተገንብቶ ለሕዝብ አገልግሎት ሲበቃ፣ የከተማዋ ነዋሪዎች የዘመናት ጥያቄ በድል የተመለሰበት ታሪካዊ ቀን ሆኗል።

ይህንን የምርቃት ስነ-ስርዓት በደብረ ማርቆስ ከተማ በይፋ የመሩት የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)፣ ልማት የሕዝብ ጥያቄን ለመመለስ ብቻ ሳይሆን፣ አገርን በጋራ ለመገንባት ያለንን ቁርጠኝነት የሚያሳይ የጋራ ተጋድሎ መሆኑን በአጽንኦት ገልጸዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በንግግራቸው መጀመሪያ ላይ የከተማዋን የቀድሞ ስም "መንቆረር" በማስታወስ የደብረ ማርቆስን ስመጥር ታሪክ ወደ ኋላ መለስ ብለው ጎብኝተዋል።

ንጉሥ ተክለ ሃይማኖት ስሟን ከፍ አድርገው፣ የጎጃም መናገሻ እና የወሎና የወለጋ ድልድይ አድርገው የሾሟት ደብረ ማርቆስ፣ በዘመኑ ለኢትዮጵያ ስልክና ቴሌግራፍ ቀድመው ከገቡላቸው ከተሞች መካከል አንዷ የነበረችበትን  ዘመን አስታውሰዋል።

ዛሬም ይህች ከተማ ያንን የቀድሞ ክብሯን ለመመለስ የሚያስችል አቅም እንዳላት የጠቆሙት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ አውሮፕላን ማረፊያው ለአካባቢው ንግድና ቱሪዝም ትልቅ መነቃቃትን እንደሚፈጥር ተስፋቸውን ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ መስፍን ጣሰውና ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ተመስገን ጥሩነህን የመሳሰሉ ከዚሁ አካባቢ የተገኙ ልጆች፣ ለትውልድ ቀዬአቸው የሰሩት ስራ የጀመረው በምኞት እንደነበር የገለጹት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ በመደመር መንፈስ አብሮ መስራትና መደጋገፍ አገርን ወደ ተሻለ ደረጃ እንደሚያሸጋግር አብራርተዋል።

በንግግራቸውም ደብረ ማርቆስ በትናንትናው ታሪኳ የልዩነት ድልድይ ሆና እንደኖረች ሁሉ፣ ዛሬም በዘርና በጎጠኝነት ከመከፋፈል ይልቅ፣ አንድነትንና መደማመጥን መምረጥ እንደሚገባ አሳስበዋል።

በየአካባቢው የተሰገሰገው የሽፍታ እንቅስቃሴ የሕዝብን ነጻነትና የልማት ጉዞ የሚያስተጓጉል በመሆኑ፣ ሁሉም ዜጋ ሰላሙን ከጸጥታ አካላት ጋር በመቀናጀት እንዲጠብቅ ጥሪያቸውን አስተላልፈዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)፣ መንግሥታቸው ለውይይትና ለጋራ መግባባት በሩ ክፍት መሆኑን በድጋሚ አረጋግጠዋል።

ኢትዮጵያ ጦርነትንም ሆነ ሰላምን በሚገባ የምታውቅ አገር በመሆኗ፣ አሁን ሊያተኩርባት የሚገባው ዋና ጉዳይ ልማትና ብልጽግና ብቻ መሆኑን አስታውሰዋል።

የታሪክ ማህደርን እያስታወሱ፣ በአሁኑ ወቅት ያለውን የዘርና የጽንፈኝነት መከፋፈል በጋራ መታገልና በአንድነት መንፈስ ለልጆች የተሻለች አገር ማስረከብ የሁላችንም አደራ መሆኑን ገልጸዋል።

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: