Search

የደብረ ማርቆስ ነዋሪዎች የዓመታት ጥያቄ በመመለሱ እንኳን ደስ ያላችሁ፡- አቶ መስፍን ጣሰው

እሑድ ሐምሌ 05, 2018 40

የደብረ ማርቆስ ንጉሥ ተክለ ሃይማኖት አውሮፕላን ማረፊያ ሲመረቅ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ መስፍን ጣሰው ባደረጉት ንግግር አየር መንገዱ ይህን ዘመናዊ አውሮፕላን ማረፊያ በማጠናቀቁ ታላቅ ኩራት እንደሚሰማው ገልጸዋል።

የደብረ ማርቆስ ነዋሪዎች ለዓመታት ሲጠይቁት የነበረው የትራንስፖርት አገልግሎት መመለሱ ትልቅ የምሥራች ነው ያሉት ዋና ሥራ አስፈጻሚው የኢትዮጵያ አየር መንገድ ከ50 ዓመታት በፊት በከተማዋ አገልግሎት ይሰጥ እንደነበር አስታውሰዋል።

ይሁን እንጂ የበረራ አገልግሎቱ ተቋርጦ በመቆየቱ ሕዝቡ ለአድካሚ የየብስ ጉዞና ለተለያዩ እንግልቶች ተዳርጎ መቆየቱንም ጭምረው ገጸዋል።

“አሁን ግን የአውሮፕላን ማረፊያው ተጠናቆ በመመረቁ ሕዝቡ በምቾትና በደኅንነት መጓዝ ይችላል” ያሉት አቶ መስፍን፣ አዲሱ አውሮፕላን ማረፊያ በቀን ሦስት ጊዜ፣ በሳምንት ደግሞ 21 መደበኛ በረራዎችን እንደሚያስተናግድ አስታውቀዋል።

ማረፊያው ቦይንግ አውሮፕላኖችን ጨምሮ ትልልቅ የሲቪል አውሮፕላኖችን ማሳረፍ የሚያስችል አቅም እንዳለውም ተገልጿል።

ለዚህ ፕሮጀክት ማጠናቀቂያ 1.4 ቢሊዮን ብር ወጪ መደረጉን የጠቆሙት ዋና ሥራ አስፈጻሚው፣ ይህ መሠረተ ልማት ለአካባቢው ኢንቨስትመንትና ቱሪዝም ትልቅ መነቃቃትን እንደሚፈጥር ተናግረዋል።

አቶ መስፍን ጣሰው አክለውም፣ የሀገርን ዕድገት የሚያፋጥኑ መሰል ፕሮጀክቶች በመላው ኢትዮጵያ ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ አረጋግጠዋል።

በመሐመድ ፊጣሞ

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: