ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በሀገራችን “ሳይረግጡት አይሰበር፣ ሳይታገሱት አይበገር” የሚለውን ብሂል በመጥቀስ፣ ማንኛውም ልማት የራሱ የሆነ ሂደትና ጊዜ እንደሚፈልግ አስታወቁ።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በደብረ ማርቆስ የንጉሥ ተክለ ሃይማኖት የአውሮፕላን ማረፊያ ምርቃት ላይ እንደተናገሩት፣ ልማት ልክ እንደ አንድ ጫጩት ከዕንቁላል ውስጥ ለመውጣት ሙቀትና ጥበቃ እንደሚያስፈልገው ሁሉ፣ በትክክለኛው ጊዜ ፍሬ እንዲያፈራ ትብብርንና ትዕግስትን ይሻል።
“ስለፈለግን ብቻ ዕንቁላሉን ያለጊዜው ብንሰብረው ጫጩት ማግኘት አንችልም፤ ልማትም እንደዚሁ በትክክለኛው ጊዜ ፍሬ አፍርቶ ለምድርና ለሰማይ ሳቅ እንዲሆን ጥበቃንና ጊዜን ይፈልጋል” ብለዋል።
ኢትዮጵያ ጥንታዊና ታሪክ ጠገብ ሀገር ከመሆኗም በላይ ሰላምንና ጦርነትን በሚገባ የምታውቅ ሀገር መሆኗን የገለጹት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ አሁን ላይ ሀገራችን የምትፈልገው ልማትን፣ ብልጽግናን፣ መደማመጥንና መከባበርን እንደሆነ አስረድተዋል።
በታሪክ ላይ ቆሞ መልካም መልካሙን በመውሰድና የጎደለውን በመሙላት ለልጆች የተሻለች ሀገር ማስረከብ እንደሚገባ ያሳሰቡት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ ወቅታዊ ችግሮችን በሰላማዊ መንገድ በመፍታት ለመለያየትና ለመገዳደል ዕድል ላለመስጠት መላው ሕዝብ በጋራ እንዲቆም በታላቅ ትሕትና ጥሪያቸውን አቅርበዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ከዓመታት በፊት በከተማዋ ተክለውት እንደነበረው ዛፍ ሁሉ፣ በደብረ ማርቆስ የንጉሥ ተክለ ሃይማኖት የአውሮፕላን ማረፊያን ቅጥር ግቢ ውስጥ ዛፍ በመትከል አረንጓዴ ዐሻራቸውን አሳርፈዋል።
ይህ ተግባር የአንድነት መበልጸግና ማበብ ምልክት እንደሆነ የገለጹት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ የነገይቱ ኢትዮጵያ ለትውልድ የተመቸች እንድትሆን ከመስራትና ከመድከም ውጪ ሌላ አማራጭ የሌለ መሆኑን አስገንዝበዋል።
በሃይማኖት ከበደ
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: