በታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ መጠናቀቅ፣ በከተሞች በተከናወነው የኮሪደር ልማት፣ በስንዴ ምርት በምግብ ራስን ለመቻል በተደረገው ጥረት እና በቅርቡ በማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያዎች ኢትዮጵያ በሁለንተናዊ የማንሠራራት ጉዞ ላይ ትገኛለች።
ኢትዮጵያ የጀመረችው ይህ ሁለንተናዊ የማንሰራራት እና የልማት ጉዞ ዘላቂነት የሚኖረው መጠላለፍን፣ ጥላቻን እና ከፋፋይ አስተሳሰቦችን በማስወገድ፤ በሕግ የበላይነት እና በጋራ ጥረት ላይ የተመሠረተ አዲስ የሥራ ባህል ሲገነባ ነው።
በየዘመናቱ እየተባባሱ የመጡ መጠላለፎች፣ ከፋፋይ ትርክቶች እና የጥላቻ ንግግሮች ሀገራዊ አቅምን በመበተን የልማት ጉዞውን ሲያስተጓጉሉ መቆየታቸው ይታወቃል።
እርስ በርስ ጣት ከመጠቋቆም እና ከመጠላለፍ ወጥቶ ለጋራ ዓላማ ላይ መሰለፍ፣ የልማት ጉዟችንን የሚያፋጥን ትልቅ ጉልበት ነው።
ልዩነቶችን በጥበብ በማስተናገድ በሀገር ሕልውና፣ ሰላም እና ልማት ላይ የጋራ መግባባት መፍጠር ከአላስፈላጊ ውዝግቦች ወጥተን ሙሉ አቅማችንን ለልማት እንድናውል ያስችለናል።
ማንኛውም የልማት እንቅስቃሴ ያለ አስተማማኝ ሰላም እና የሕግ የበላይነት መረጋገጥ ዘላቂ ፍሬ ሊያፈራ አይችልም።
ስለሆነም የሕግ የበላይነትን ማረጋገጥ የዜጎችን ደኅንነት የሚጠብቅ፣ ፍትሐዊ አሠራርን የሚያሰፍን እና ለኢንቨስትመንት አስቻይ ሁኔታ የሚፈጥር ነው።
በሌላ በኩል ግለሰባዊ አሠራሮችን በጠንካራ እና ገለልተኛ ተቋማዊ አሠራሮች መተካት የሙስና እና የመልካም አስተዳደር እክሎችን ለመቅረፍ መሠረት ይሆናል።
ታዲያ የኢትዮጵያ አዲሱ የዘመን ገጽ በብሩህ ተስፋ የሚጻፈው እያንዳንዱ ዜጋ አዲሱን የለውጥ እና የሥራ ባህል ሲላበስ ነው።
በንግግር እና በቃላት ብቻ ከመወሰን ይልቅ በየተሰማራንበት መስክ በተግባር፣ በፈጠራ እና በላብ የተደገፈ ውጤት ማምጣት አዲሱ የዜግነት መስፈርት ይሆናል።
አካባቢያዊ አስተሳሰቦችን ከሀገራዊ ራዕይ ጋር በማስማማት በጋራ የመሥራት፣ ጥራትን እና የጊዜ አጠቃቀምን የማክበር አዲስ ሀገራዊ የፈጠራ እና የሥራ ምህዳር እየተገነባ ይገኛል።
ትናንት ያጋጠሙንን ፈተናዎች ተሻግረን ወደፊት ለመራመድ አሮጌውን እና የማይጠቅመውን አስተሳሰብ አውልቆ መጣል ወሳኝ ነው።
በዚህም ምክንያት ኢትዮጵያ ጠንካራ ተቋማት እንዲኖሩ ለትውልድ የሚተላለፍ መሠረት እየጣለች ትገኛለች።
በጠንካራ ሪፎርም እና በምክክር፣ የፀጥታ እና ደኅንነት ተቋማትን እና የፍትሕ ዘርፉን የማጠናከር ሥራ በስፋት እየተሠራ ነው።
በፖለቲካው መስክም ሁሉም የሀገር ባለቤት እንዲሆን ምህዳሩ ተከፍቷል፤ ሜዳውን ለሀገር በሚጠቅም መልኩ መጠቀም ግን የሕግ የበላይነትን ታሳቢ ያደረገ የፖለቲከኞች ዋነኛ ሥራ ነው።
በሕግ የበላይነት፣ በብሔራዊ መግባባት እና በአዲስ የሥራ ባህል የሚመራው ይህ የጋራ ጉዞ ኢትዮጵያን ወደሚመጥናት የከፍታ ማማ የሚያሻግራት ጠንካራ መሠረት ነው።
በሐና ምንዳሁን
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: