የዓለም የፖለቲካ እና የኢኮኖሚ ታሪክ በግልጽ እንደሚያስተምረን፤ ታላላቅ ሀገራት እና ሥልጣኔዎች ከገቡበት መዋቅራዊ ማነቆ እና የታሪክ አዙሪት መውጣት የቻሉት፣ ርዕዮተ-ዓለማዊ ግትርነትን ሰብረው ነባራዊውን የሀገር እውነታ መሠረት ባደረገ 'ተግባራዊ' (ፕራግማቲክ) ፍልስፍና መመራት ሲጀምሩ ነው።
በ20ኛው ክፍለ ዘመን የተከናወነው የቻይና የለውጥ ጉዞ እና በ21ኛው ክፍለ ዘመን እየተተገበረ ያለው የኢትዮጵያ የሪፎርም መንገድ፣ በሁለት የተለያዩ ዘመናት እና መልክዓ ምድሮች ውስጥ የተከሰቱ ቢሆኑም፣ እጅግ አስገራሚ የሆኑ ታሪካዊ፣ ፍልስፍናዊ እና ስትራቴጂያዊ መመሳሰሎች አሏቸው።
የሁለቱም ሀገራት የለውጥ ታሪክ የሚያስተምረን ዋናው ቁምነገር፤ አንዲትን ሀገር ከተዘጋ እና ከተወጠረ ሥርዓት አውጥቶ ወደ አዲስ የኢኮኖሚ እና የማኅበራዊ ግስጋሴ ማሸጋገር የሚቻለው፣ በመሬት ላይ ባለው እውነታ ላይ በተመሠረተ ሥርዓታዊ ዕድሳት መሆኑን ነው።
ቻይና ታሪካዊው 'የባሕል አብዮቷ' ካበቃ በኋላ፣ የነበረውን የኮሚኒስት ፓርቲ መዋቅር አላፈረሰችውም። ይልቁንም መዋቅሩን ለአዲስ የኢኮኖሚ ራዕይ እንዲያገለግል አድርጋ ዳግም ቀረፀችው።
ኢትዮጵያም በተመሳሳይ፣ ሀገራችንን ለውድቀት ዳርጎ የነበረውን የፖለቲካ እና የኢኮኖሚ ማነቆ ለመፍታት የመረጠችው አፍርሶ የመገንባትን የጥፋት አዙሪት ሳይሆን፣ ነባሩን አቅም ጠብቆ እና አጎልብቶ ሀገር የማስቀጠል፣ ስህተትን የማረም እና ጉድለትን የመሙላት የመጠገን መንገድ ነው።
የ'መደመር' ፍልስፍና መሠረታዊ መርሕም ይኼው ነው፦ ሥርዓቱ የተሰበሩበትን መዋቅራዊ፣ ፖለቲካዊ እና ኢኮኖሚያዊ ክፍተቶች በመለየት መጠገን።
ሥርዓትን ሳያፈርሱ ሙሉ ለሙሉ ማደስ መቻሉ፣ ሁለቱም ሀገራት በለውጥ ማዕበል ውስጥ ሆነው ሀገራዊ አንድነታቸውን እንዳያጡ እና ወደ ቀውስ እንዳያመሩ ትልቅ መከታ ሆኗቸዋል።
የቻይና የለውጥ ፍልስፍና ማጠንጠኛ 'ፕራግማቲዝም' ነበር። ቻይና "አይጧን እስከያዘች ድረስ ድመቷ ጥቁርም ሆነች ነጭ ለውጥ የለውም" ወደሚል ዝነኛ ሀገራዊ ብሂል በመሸጋገር፣ ፖሊሲዎች መመዘን ያለባቸው በንድፈ-ሐሳባዊ ንጽሕናቸው ሳይሆን፣ በመሬት ላይ በሚያመጡት የኢኮኖሚ ዕድገት መሆን እንዳለበት አሰመረች።
የኢትዮጵያ 'መደመር' ፍልስፍና ይህንኑ ተግባራዊነት ይጋራል። ኢትዮጵያ ለግማሽ ምዕተ ዓመት ከተተበተበችበት የግራ ዘመም ርዕዮተ-ዓለም፣ የዜሮ-ድምር ፖለቲካ፣ የብሔር ጽንፈኝነት እና የተቃርኖ ትርክት በመውጣት፤ ጠቃሚ ሀገራዊ አቅሞችን አዋህዳ ወደ አንድ ግብ የሚያሰባስብ አማካይ መንገድን ተከትላለች።
በኢኮኖሚው ዘርፍ የቻይና ትልቁ ትሩፋት እ.አ.አ በ1978 የጀመረችው “የኢኮኖሚ ሪፎርም እና ክፍት ማድረግ” ፖሊሲ ነው። ቻይና የውጭ ኢንቨስትመንትን በመሳብ እና የግል ዘርፉን በማበረታታት ከ600 ሚሊዮን በላይ ዜጎቿን ከድህነት አውጥታለች። አካሄዷም "ድንጋይ እየረገጡ ወንዝ መሻገር" በሚል በልዩ የኢኮኖሚ ቀጠናዎች እየሞከሩ የማስፋፋት ስልት ነበር።
በኢትዮጵያ የተተገበረው 'ሀገር በቀል የኢኮኖሚ ሪፎርም' ተቀራራቢ ቢሆንም፣ የራሱ ልዩ ባሕርይ አለው። የኢትዮጵያ ፕራግማቲዝም ማኅበረ-ፖለቲካዊ ትሥሥር የመጠገን ጥልቅ ተልዕኮ ሲኖረው፤ አካሄዱም የቻይናን 'እየሞከሩ የማለፍ' ስልት ሳይሆን፣ የመፍጠን እና የዝላይ (Leapfrog) መንገድ ነው።
እየተተገበረ ያለው የማክሮ-ኢኮኖሚ ፖሊሲ ማሻሻያም ለዚህ ማሳያ ሲሆን፣ ኢትዮጵያ መንግሥት ከተቆጣጠረው ኢኮኖሚ በመውጣት የግል ዘርፉን ወደ መሪነት እያሸጋገረች ነው።
በግብርናው ዘርፍም ቻይና ያደረገችው ማሻሻያ ለኢንዱስትሪዋ መነሣት መሠረት እንደነበር ሁሉ፣ ኢትዮጵያም በተመሳሳይ የግብርና አብዮት በማካሄድ በታሪኳ ለመጀመሪያ ጊዜ በስንዴ ምርት ራሷን ችላ ወደ ውጭ ገበያ መላክ ችላለች።
ከዚህ ጎን ለጎንም፣ "ኢትዮጵያ ታምርት" በሚል ሀገራዊ ንቅናቄ የኢንዱስትሪ የማምረት አቅሟን እያጎለበተች ይገኛል። ሆኖም የኢትዮጵያ ጉዞ የቻይናን ሞዴል እንዳለ የመገልበጥ ሒደት አይደለም። ቻይና ኢኮኖሚዋን በዝግታ ለመክፈት ያገኘችውን ሰፊ ጊዜ ኢትዮጵያ አሁን ላይ አታገኘውም።
በመሆኑም ኢትዮጵያ ኢኮኖሚዋን ክፍት የማድረግ (Liberalization) ሪፎርምን፣ እንዲሁም በዲጂታላይዜሽን እና ፈጠራ ዘርፍ ታላቅ እመርታ የማድረግ ግዳጅን በአንድ የታመቀ ጊዜ ውስጥ ተሸክማለች። ይህ ድርብ ኃላፊነት ሀብትን፣ ጊዜን እና ዕውቀትን ያለ ብክነት መደመርን ግድ ይላል።
ለውጥ በአንድ ጀምበር የሚያልቅ ሳይሆን ቋሚነትን እና ተለዋዋጭነትን አዋህዶ ሊቀጥል የሚገባው ሒደት ነው። በዚህ ሒደት የ'መደመር' ፍልስፍና ጥልቀት የሚገለጠው፣ ትናንት የተሠሩ መልካም ዕሴቶችን በማስቀጠል እና ሀገርን ወደ ኋላ ሲጎትቱ የነበሩ ስብራቶችን ደግሞ በማረም እና በመጠገን ወጥ የሆነ ሀገራዊ ማንነትን በመገንባቱ ላይ ነው።
የኢትዮጵያ እና የቻይና የሪፎርም እርምጃዎች ግብ ጊዜያዊ የፖለቲካ መረጋጋትን ማምጣት ብቻ ሳይሆን፣ ታላላቅ ሕዝቦችን ወደ ታሪካዊ የሥልጣኔ ከፍታቸው የመመለስ ብሔራዊ ራዕይ ነው።
የቻይና ሪፎርም ቻይናን ወደ ቴክኖሎጂ እና ዕድገት ጫፍ እንዳደረሳት ሁሉ፣ የኢትዮጵያ የለውጥ ጉዞም የነገዋን የበለጸገች ሀገር የመገንባት ስትራቴጂ ነው።
ርዕዮተ-ዓለማዊ ዶግማን ሰብሮ በተግባራዊነት መመራት እንዲሁም አግላይነትን ትቶ በመደመር ሀገራዊ አቅምን ማሰባሰብ፣ ሀገራትን ከውድቀት አፋፍ መልሰው ታሪክ ሠሪ እንደሚያደርጋቸው የሁለቱ ሀገራት ተሞክሮ ሕያው ምሥክር ነው።
የኢትዮጵያ ሪፎርም የመጨረሻ ግብም የተበታተነውን አቅም አሰባስቦ፣ ዜጎቿ በነጻነት የሚኖሩባትን፣ በዓለም አቀፍ መድረክ ተጽዕኖ ፈጣሪ የሆነች እና ከድህነት ወደ ብልጽግና የተሸጋገረች ጠንካራ ኢትዮጵያን መገንባት ነው።
በአዶኒያስ ወልደአረጋይ
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: