በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል፣ ጎፋ ዞን፣ መሎኮዛ ወረዳ ለመንገድ መሠረተ ልማት እና ለግብርና ልማት አገልግሎት ከ343 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ ወጥቶባቸው የተገዙ ማሺነሪዎች ለአገልግሎት ዝግጁ ሆነዋል።
በስፍራው ተገኝተው መልዕክት ያስተላለፉት የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ጥላሁን ከበደ፥ ለ1 ማሽን ግዢ የተጀመረው እንቅስቃሴ 11 ማሽነሪዎችን መውለዱ ስንተባበር የተሻለ ውጤት ማስመዝገብ እንደምንችል ያሳየ ስኬት ነው ሲሉ ገልጸዋል።
የማሽነሪዎቹ ግዢ በለም መሬቱ እና በትርፍ ምርቱ ለሚታወቀው የመሎኮዛ ወረዳ የብልጽግና ትልምን ለማሳካት በር ከፋች ናቸው ብለዋል።
ማሽነሪዎቹን በፍጥነት ወደ ሥራ ማስገባት እና በአግባቡ ማስተዳደር ውጤታማ ሥራ ለማከናወን ቀጣይ የቤት ሥራ ሊሆን ይገባል ሲሉ አሳስበዋል።
የጎፋ ዞን ዋና አስተዳዳሪ ዳግማዊ አየለ (ኢ/ር) በበኩላቸው፥ የማሽነሪዎቹ ግዢ በእጃችን ያለውን ሀብት እና ፀጋ በቅንጅትና በአግባቡ ከተጠቀምን፣ ተዓምር መሥራት እንደምንችል ማሳያ ነው ብለዋል።
በቀጣይም ብልጽግናችንን ለማረጋገጥ የተፈጥሮ ሀብት እና የሰው ኃይል ፀጋዎቻችንን በተቀናጀ መንገድ መጠቀም እንደሚያስፈልግ ጠቁመዋል።
ማሽነሪዎቹ የልማት ሥራዎቻችን ማሳለጫ በመሆናቸው በአግባቡ በመጠቀም ተጨማሪ ሀብት ማፍራት ያስፈልጋል ሲሊ አሳስበዋል።
እያንዳንዱ የአካባቢው ነዋሪ ዶሮ በመሸጥ ጭምር ገንዘብ አዋጥቶ ትራክተር መግዛቱን የተናገሩት የአካባቢው ነዋሪዎች፣ በማሽነሪዎቹ ግዢ የተሻለ ተስፋ መሰነቃቸውን ተናግረዋል።
በተመስገን ተስፋዬ
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: