የለውጥ ጉዞ በከተሞች በሚገነቡ ግዙፍ ሕንፃዎች ወይም በተዘረጉ ዘመናዊ መንገዶች ብቻ አይገለጽም። እውነተኛው እና ዘላቂው የልማት ታሪክ የሚጻፈው በሰፊው ማሳ፣ በአርሶ አደሩ ላብ እና በአፈር ውስጥ በሚዘራ ምርታማ ዘር ነው፤ ዛሬ በኢትዮጵያ እውን እየሆነ ያለው ነባራዊ እውነትም ይኸው ነው።
ግብርና የኢኮኖሚያችን ማዕከል እና የብዙኃን ሕይወት መሠረት በመሆኑ በዘርፉ የሚመዘገብ አዎንታዊ ለውጥ ከምርት መጨመር አልፎ ለምግብ ሉዓላዊነት መረጋገጥ እንዲሁም ለኢኮኖሚ ጥንካሬ የሚያበረክተው አስተዋጽኦ የጎላ ነው።
ዛሬ በስንዴ፣ በቡና፣ በአቮካዶ እና በሌሎች ምርቶች ላይ እየታየ ያለው መጠነ-ሰፊ እንቅስቃሴ የዚህ እውነት ግልጽ ማሳያ ነው።
በተለይም የስንዴ ምርትን በከፍተኛ ደረጃ ማሳደግ የኢትዮጵያ ተጨባጭ የብልጽግና ጉዞ ማረጋገጫ ሆኗል።
በበጋ የመስኖ ስንዴ ልማት የታየው ተዓምር ከስንዴ አስመጪነት ወደ ላኪነት የተሸጋገርንበትን አዲስ የታሪክ ምዕራፍ ከፍቷል።
ከ3 ሚሊዮን ሄክታር በላይ መሬትን በመስኖ በማልማት፣ አርሶ አደሩን በክላስተር አደራጅቶ በማረስ፣ ዘመናዊ የእርሻ መሳሪያዎችን በማስፋፋት እና ምርጥ ዘርን በመጠቀም የተመዘገበው ከፍተኛ የምርት መጠን የምግብ ፍላጎትን በራስ አቅም የመሸፈን ራዕይን እውን አድርጓል።
ቡና ደግሞ የኢኮኖሚ አምድ ብቻ ሳይሆን የባህል እና የማንነት መለያችን ነው። ከማሳ እስከ ዓለም አቀፍ ገበያ ድረስ ያለውን የምርት ሰንሰለት ማዘመን፣ የጥራት ቁጥጥርን ማጠናከር እና ቀጥታ የገበያ ትስስር መፍጠር የተቻለ ሲሆን፣ በዚህም በዓመት ከቡና ኤክስፖርት የሚገኘውን የውጭ ምንዛሬ ከ3.1 ቢሊዮን ዶላር በላይ በማድረስ አዲስ ታሪክ ተመዝግቧል።
ከዚህ ጎን ለጎን የሌማት ትሩፋት በሚል ሀገራዊ ንቅናቄ የፍራፍሬ፣ በተለይም የአቮካዶ፣ የእንስሳት እና የማር ልማትን በማስፋፋት የሥርዓተ ምግብ ዋስትናን ከማረጋገጥ ባለፈ አርሶ አደሩን የገበያ ተጠቃሚ ማድረግ ተችሏል።
የግብርናውን ዘርፍ ማዘመን ያለ ቴክኖሎጂ እና ያለ ዘመናዊ አሠራር አይታሰብም። መንግሥት የግብርና ማሽነሪዎችን ከቀረጥ ነፃ ወደ ሀገር ውስጥ እንዲገቡ ባደረገው የፖሊሲ ማሻሻያ የትራክተር እና የኮምባይነር አቅርቦት በከፍተኛ ደረጃ አድጓል።
የመስኖ መሠረተ ልማቶችን ማስፋፋት፣ የአፈር አሲዳማነትን ማከም እና ዲጂታል አሠራሮችን ማስገባት የአርሶ አደሩን ድካም ከመካስ ባለፈ የምርት ብክነትን ቀንሷል።
የገጠሩን ግብርና ከባህላዊ እና ዝቅተኛ ምርታማነት ወደ ዘመናዊ የንግድ ግብርና ማሸጋገር የዘላቂ ዕድገት ዋስትና መሆኑን በተግባር እያየን እንገኛለን።
ከሁሉም በላይ የዚህ ለውጥ ታሪክ ዋና ባለቤት አርሶ አደሩ ነው። በማሳ ላይ የሚዘራው ዘር ወደተትረፈረፈ ምርት ሲቀየር፣ የአርሶ አደሩ ጥረት እና ላብ ደግሞ ወደ ብልፅግና ይለወጣል።
ግብርናን ማዘመን ማለት ምርትን ማሳደግ ብቻ ሳይሆን የዜጎችን ሕይወት ማሻሻል እና የኢትዮጵያን የኢኮኖሚ ሉዓላዊነት ማረጋገጥ ማለት ነው።
ዛሬ በስንዴ ማሳዎች ላይ የሚስተዋለው ፍሬያማ ሰብል፣ በቡና እና ፍራፍሬ እርሻዎች ላይ የሚታየው ተስፋ የነገዋን ሙሉ በሙሉ በራስ አቅም የቆመች ታላቅ ኢትዮጵያ መሠረት እየጣለ ነው።
በማሳ የሚዘራው ዘር የምርት ብቻ ሳይሆን የብሔራዊ ክብር፣ የምግብ ሉዓላዊነት እና የብሩህ ነገአችን ዋስትና ነው።
በኢንቲሃድ አብራር
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: