Search

የብልጽግና ፓርቲ ወጣቶች ክንፍ በዚምባብዌ እና በናይጄሪያ ታሪካዊ የአረንጓዴ ዐሻራ የችግኝ ተከላ አካሄደ

ቅዳሜ ነሐሴ 30, 2018 78

የኢትዮጵያ አረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብር አካል የሆነው እና "የአፍሪካ ወንድማማችነትን እንትከል" በሚል መሪ ቃል የሚካሄደው የሁለተኛ ዙር መርሐ ግብር በዚምባብዌዋ ሀራሬ እና በናይጄሪያዋ አቡጃ ከተሞች በድምቀት ተካሄደ።

የብልጽግና ፓርቲ ወጣቶች ክንፍ አመራር አባላት ከሁለቱ ሀገራት ገዢ ፓርቲዎች የወጣቶች ሊግ አመራሮች ጋር በመሆን ይህንን ታሪካዊ የጋራ የችግኝ ተከላ አከናውነዋል።

በዚምባብዌ ርዕሰ መዲና ሀራሬ በተካሄደው መርሐ ግብር፣ ስድስት አባላት ያሉት የብልጽግና ፓርቲ የወጣቶች ክንፍ ልዑክ ከዚምባብዌው ገዢ ፓርቲ (ZANU-PF) ወጣቶች ሊግ ጋር በመተባበር ከኢትዮጵያ የወሰዷቸውን ሀገር በቀል ችግኞች "አፍሪካን ሄሪቴጅ ፓርክ" ውስጥ በጋራ ተክለዋል።

የልዑኩ መሪ አቶ ሰንበቱ አበባ፣ ኢትዮጵያ ላለፉት ስምንት የለውጥ ዓመታት በአረንጓዴ ዐሻራ ያስመዘገበቻቸውን ዐበይት ስኬቶች እና መርሐ ግብሩ ለአህጉሪቱ ያለውን ፋይዳ አብራርተዋል።

በተመሳሳይ በናይጄሪያ አቡጃ ከተማ በተከናወነው የአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብር፣ የናይጄሪያ ገዢ ፓርቲ (APC) የወጣቶች ሊግ ሊቀ መንበር / ዳዮ አብዱላሂ እስራኤል ለኢትዮጵያውያኑ ልዑካን አቀባበል አድርገዋል።

ሊቀ መንበሩ በንግግራቸው፣ በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (/) የተጀመረው ይህ የአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብር አህጉራዊ ፋይዳ ያለው እና በመላው አፍሪካ ደረጃ ሊተገበር የሚገባው አርአያነት ያለው ተግባር መሆኑን አድንቀዋል።

በናይጄሪያ የብልጽግና ፓርቲ ወጣቶች ልዑክ መሪ አቶ ገዛኸኝ አንዳርጌ በበኩላቸው፣ ስለ አረንጓዴ ዐሻራው ሀገራዊ ስኬት እና አህጉራዊ ትሩፋት ለተሳታፊዎች ሰፊ ማብራሪያ ሰጥተዋል።

መርሐ ግብሩ አፍሪካውያን ወጣቶች የአየር ንብረት ለውጥን በጋራ ለመቋቋም ያላቸውን ቁርጠኝነት ከማሳየት ባለፈ፣ የፓን-አፍሪካኒዝም አንድነትን በተግባር ያረጋገጠ መሆኑ ተመላክቷል።

ይህ የጋራ የአካባቢ ጥበቃ ተግባር በኢትዮጵያ፣ በዚምባብዌ እና በናይጄሪያ መካከል ያለውን ስትራቴጂያዊ እና ታሪካዊ ግንኙነት ይበልጥ የሚያጠናክር ሲሆን፣ የኢትዮጵያን የአረንጓዴ ዐሻራ ራዕይ ወደ አህጉራዊ ደረጃ የሚያሸጋግር ወሳኝ እርምጃ መሆኑ የብልጽግና ፓርቲ /ቤት አስታውቋል።

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: