Search

የማይበገረው ወኔ፦ የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት ብቃት

ማክሰኞ ጳጉሜን 03, 2018 43
የአንድ ሀገር የመጨረሻው ምሽግ እና የሉዓላዊነቷ የጀርባ አጥንት መከላከያ ሠራዊት ነው። የኢትዮጵያ ሠራዊትም የራሱ ዶክትሪን ያለው፣ ዓላማውን የሚያውቅ እና ከመንደርተኝነት የጸዳ በመሆኑ እንደ ፖለቲካው አየር ንብረት ወደ ነፈሰበት ሁሉ የሚነፍስ ተቋም አለመሆኑን በተግባር እያሳየ ይገኛል።
የፖሊሲን አቅም ተሻግረው በኃይል እና በጠመንጃ ፍላጎታቸውን ለመጫን የሚሞክሩ የውስጥ ጽንፈኛ ኃይሎችን መመከት እና ሥርዓት ማስያዝ የሠራዊቱ ሕገ መንግሥታዊ ግዴታ እንጂ የፖለቲካ ትርምስ ሲፈጠር "ካምፕ ገብቶ" የሚመለከትበት አሠራር በየትኛውም ዓለም የለም። የሠራዊቱ ወቅታዊ ቁመና ከምንጊዜውም በላይ ሀገራዊ ጸጥታን በማስከበር ረገድ አስተማማኝ ደረጃ ላይ መድረሱን ያሳያል።
ሠራዊቱ የውስጥ ጸጥታ እና ሰላምን የማረጋገጥ ግዳጅ ከመወጣት እና የሀገር ዳር ድንበርን ከማስከበር ባሻገር የኢትዮጵያን ወታደራዊ ዲፕሎማሲ ወደ ላቀ ደረጃ እያሸጋገረው ይገኛል። በአፍሪካም ሆነ በዓለም አቀፍ ደረጃ ያለው ተቀባይነት እና ክብር ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ መጥቷል።
በአሁኑ ጊዜ ጎረቤት እና ሌሎች የአፍሪካ ሀገራት የኢትዮጵያን ወታደራዊ ልምድ ለመቅሰም፣ ኃይላቸውን ለማሠልጠን እና ተሞክሮ ለመለዋወጥ ከፍተኛ ፍላጎት እያሳዩ ነው።
የጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ ይህንን የሠራዊቱን ዓለም አቀፋዊ ተወዳዳሪነት እና ልዩ ጽናት ሲገልጹ፣ "እንደ ኢትዮጵያ ዓይነት ሠራዊት አሁን ዓለም ላይ አለ ብዬ አላምንም። ብዙ ሚሳኤል፣ ብዙ ጄት፣ ብዙ ትጥቅ፣ ብዙ ደመወዝ የሚከፈለው ወታደር ሊኖር ይችላል። የኢትዮጵያ ዓይነት ግን ተልእኮን በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ መፈጸም የሚችል፣ ችግር ተቋቁሞ ሀገሩን የሚያስቀድም የለም" በማለት የሠራዊቱን ወደር የለሽ ጀግንነት ገልጸዋል።
የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት ብቃት እና ወታደራዊ ወኔ ከዘመናዊ ትጥቅ እና ቴክኖሎጂ ባሻገር በእልህ፣ በእምነት እና በማይነጥፍ የሀገር ፍቅር ስሜት ላይ የታነጸ ነው። ጀግንነት የኢትዮጵያ ወታደር መገለጫ ብቻ ሳይሆን የታሪክ ማኅተሙ ጭምር በመሆኑ በበረሃ ሐሩር እና በተራራ ቁር ሳይበገር፣ ረኃብ እና ጥማትን ታግሶ ድልን የመቀዳጀት ልዩ ወደር የለሽ ጀግንነት አለው።
ይህ ሥነ-ልቦናዊ ልዕልና፣ ሞትን ንቆ ሀገርን የማዳን ወኔ እንዲሁም ከዐለት የተቀረፀ የሚመስለው የሠራዊቱ ጽናት ኢትዮጵያን ከገጠሟት የሕልውና ፈተናዎች ሁሉ በድል እንድትሻገር አስችሏታል። ሠራዊቱ ጠላትን በመሣሪያ ብቻ ሳይሆን በዓላማ ጽናት እና በሞራል ብልጫ የማንበርከክ ወታደራዊ ስብዕናን በተግባር እያስመሰከረ ይገኛል።
በተጨማሪም ሠራዊቱ ከጊዜ ወደ ጊዜ እያጎለበተ የመጣው የማድረግ አቅሙ እና የውጊያ ዝግጁነት ከየትኛውም ሀገራዊ እና ቀጣናዊ ሥጋት በላይ አግዝፎታል። ጀግንነት በደመ ነፍስ ሳይሆን በስሌት፣ ወኔ ደግሞ በተራቀቀ ወታደራዊ ቴክኖሎጂ እና የስትራቴጂ ጥበብ ሲታጀብ የሚፈጥረውን የማይበገር አቅም ሠራዊቱ በሚገባ ተላብሷል።
ከውስብስብ የመረጃ አሰባሰብ እስከ ፈጣን የኃይል ስምሪት እንዲሁም ዒላማውን ከማይስት የተቀናጀ ዘመናዊ ዕርምጃ የመውሰድ ብቃቱ ሠራዊቱን የዘመኑ የውጊያ አውድ ባለቤት አድርጎታል። ይህ አዲስ ከፍታ እና የማድረግ አቅሙ ነው እንግዲህ የሀገር ሉዓላዊነት አስተማማኝ ደረጃ ላይ ያደረሰው።
ይህ የጽናት እና የጀግንነት ታሪክ በአጋጣሚ የተፈጠረ ሳይሆን ከ1927 ዓ.ም ጀምሮ በኢትዮጵያ ወታደራዊ አካዳሚ (የቀድሞው የሆለታ ገነት ጦር ትምህርት ቤት) እና መሠል የጀግኖች ማፍለቂያ ተቋማት ውስጥ በተገነባ ጠንካራ ወታደራዊ ሳይንስ ላይ የተመሠረተ ነው።
በተለይም በአሁኑ ወቅት የውጊያ አውዱ ከመደበኛ ጦርነት ባለፈ ወደ ብዙ አውዶች ያደገ በመሆኑ ሠራዊቱ ቴክኖሎጂን የተላበሱ፣ ነባራዊ ሁኔታውን የሚረዱ እና ሥነ-ልቦናዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እንዲሁም የሳይበር ጥቃቶችን መመከት የሚችሉ መኮንኖችን በጥራት እያፈራ ይገኛል።
የኢትዮጵያ ሠራዊት ወቅታዊ ቁመና ሀገርን ከማፍረስ አደጋ የታደገ እና ለቀጣይ የዕድገት እና የብልጽግና ጉዞ መሠረት የጣለ መሆኑ አያጠያይቅም። ሆኖም ይህንን ሀገራዊ ጽናት ለማስቀጠል የፖለቲካ ልሂቃኑ ሚና ወሳኝ ነው። ኢትዮጵያን የጦርነት እና የትርምስ አዙሪት ውስጥ ከሚያስገቡ አፍራሽ ትርክቶች በመውጣት፣ ገንቢ አስተሳሰብን ማዳበር የግድ ይላል።
"እኛ 60 ዓመት እየተጣላን ነው የኖርነው። ስለ መተኮስ፣ በጉልበት ስለመቆጣጠር፣ ሌላውን ስለመጥላት ነው የተሰበክነው። ሕዝቡ ይህን በደንብ መረዳት አለበት... ይህ መቆም አለበት" ሲሉ ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ በተለያዩ መድረኮች ላይ የተናገሩት አባባልም የዚሁ ገንቢ ሀገራዊ ጥሪ ማሳያ ነው።
በበረከት ሽመልስ

 

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: