Search

የብዝኃነትና የኅብር ጥንካሬ፡ ለኢትዮጵያ ታሪካዊ ስኬቶች እና ዘላቂ ብልጽግና መሠረት

ረቡዕ ጳጉሜን 04, 2018 30

ኢትዮጵያ በብዙ ኅብረ ቀለማት የተሸለመች፣ የበርካታ ብሔር ብሔረሰቦች፣ ባህሎች እና እምነቶች መኖሪያ ድንቅ ሀገር ናት።

በረጅም የታሪክ ጉዞ ውስጥ የብዝኃነታችን እና የአንድነታችን መጋመድ ለህልውናችን እና ለስኬቶቻችን ዋነኛ ምሰሶ ሆኖ አገልግሏል።

ብዝኃነትን በአግባቡ ማስተናገድ እና በኅብረት መቆም እስከዛሬ ላስመዘገብናቸው ታላላቅ ድሎች መሠረት እንደሆነ ሁሉ፣ ለነገዋ ዘመናዊ እና የበለጸገች ኢትዮጵያ ግንባታም የማይተካ አቅም ነው።

በታሪካችን ዓለምን ያስደመሙ እና ዘመናትን የተሻገሩ አንጸባራቂ ድሎች በሙሉ የሕዝቦች የተቀናጀ ጥረትና የጋራ ትግል ውጤቶች ናቸው።

እንደ ዓድዋ ያሉ ሀገራችንን የነፃነት እና የኩራት ምልክት አድርገው ያስቀጠሉ ታሪካዊ ክንውኖች የተመዘገቡት፣ ከሰሜን እስከ ደቡብ፣ ከምሥራቅ እስከ ምዕራብ ያሉ ሕዝቦች በተለያየ ማንነታቸው ውስጥ ሆነው ለጋራ ህልውና በአንድነት በመቆማቸው ነው።

ይህ መከፋፈል የሌለበት የጋራ መስዋዕትነት ያልተሸነፈ እና የማይበገር አቅም ፈጥሯል።

ይህ የብዝኃነታችን ጥንካሬ በጦር ግንባር ብቻ ሳይሆን በዘመናዊ የልማት መስኮች፣ በስፖርት፣ በኪነ ጥበብ እና በባህል መድረኮችም ጎልቶ የሚታይ እውነታ ነው።

በዓለም አቀፍ አደባባዮች የኢትዮጵያ ሰንደቅ ዓላማ ከፍ ብሎ ሲውለበለብ ከጀርባው ያለው ሚስጥር የሁሉም ዜጎች የተቀናጀ ጥረት እና ድጋፍ ነው።

የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ ስኬት እና የአረንጓዴ ዐሻራ መርሐግብር ውጤቶች የሚያረጋግጡት፣ የተለያዩ ቋንቋዎች እና ወጎች ባለቤት የሆኑ ዜጎች ሀብት እና ጉልበታቸውን አስተባብረው ሲነሱ ታላቅ ሀገራዊ ስኬት ማምጣት እንደሚችሉ ነው።

በአሁኑ ወቅት በመደመር ዕሳቤ የተቃኘው የልማት አቅጣጫ ሰብዓዊነትን ማዕከል ማድረጉ እና የብዝኃነትን እሴት ማጎልበቱ ለዘላቂ ዕድገት አዲስ ተስፋን ፈንጥቋል።

ልማት የሚለካው በሕንፃዎችና በመሠረተ ልማቶች ግንባታ ብቻ ሳይሆን፣ በመጀመሪያ ደረጃ የዜጎችን ክብር፣ ደኅንነት እና ተጠቃሚነት ማረጋገጥ ሲቻል ነው።

የሰውን ልጅ ማዕከል ያደረገው እና በመደመር እሳቤ የሚመራው የልማት አቅጣጫ እኩልነትን፣ ፍትሕን እና የሕዝቦችን አብሮነት በማጠናከር ኢትዮጵያን ወደተሻለ የብልጽግና ምዕራፍ ያሸጋግራታል።

የብዝኃነታችን እና የኅብረታችን ጥንካሬ ትናንት ላስመዘገብናቸው ስኬቶች መሠረት እንደነበረ ሁሉ፣ ወደፊትም ልዩነቶቻችንን የውበት እና የጥንካሬ ምንጭ በማድረግ ለጋራ ብልጽግናችን መሥራት የዘመኑ ትልቁ ጥሪያችን ነው።

በሔዋን ጌታቸው

 

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: