የሰው ልጅ በትብብር እና በኅብር ሲቆም የማይፈታው ችግር፣ የማይሻገረው ሸለቆ አይኖርም።
የኅብር ቀን ሲከበር በተለይ በአዲስ አበባ ከተማ ከምንጊዜውም በላይ ጎልቶ የሚወጣው እውነት ቢኖር መዲናችን ከረጅም ጊዜ የጉራማይሌ ገጽታዋ ወጥታ ለነዋሪዎቿ ሁሉ እኩል የምትመች፣ ድጋፍ ለሚሹት ደግሞ እጇን የዘረጋች ከተማ እየሆነች መምጣቷ ነው።
አዲስ አበባ ለዘመናት ታላላቅ ፎቆች እና ዘመናዊ ሕንፃዎች ብቻ የሚታዩባት ከተማ ሳትሆን ከነዚህ ግዙፍ ሥልጣኔዎች ጀርባ ተደብቀው የነበሩ የደቀቁ እና ለሰው ልጅ ክብር የማይመጥኑ መንደሮች የነበሩባት ከተማ ነበረች።
ዓለም አቀፍ የዲፕሎማቲክ ማዕከልነቷ እንዳለ ሆኖ ስሟን የሚመጥን ዕድገት ስትናፍቅ የቆየችው መዲናችን ዛሬ ላይ በበጎ ፈቃደኝነት እና በጋራ ርብርብ የሰው ተኮር ፕሮጀክቶች እየተገነቡባት የምትገኝ የርኅራኄ ማዕከል ሆናለች።
በዚህም ለአረጋውያን፣ የሀገር ባለውለታዎች እና ማኅበራዊ ድጋፍ የሚሹ ዜጎች የዘመናዊ መኖሪያ ቤት ባለቤት መሆናቸው፣ ልማት እውነተኛ ትርጉም የሚኖረው ከሰው ልጅ ሕይወት መለወጥ ጋር ሲቆራኝ መሆኑን በተግባር ያረጋገጡ ናቸው።
ልማት የነዋሪውን የኑሮ ጫና ከማቃለል ይጀምራል በሚል መርሕ የተተገበሩት ሰው ተኮር ሥራዎች የከተማዋን ነዋሪ ተስፋ ያለመለሙ እና በኅብረታችን ምን ያህል ርቀት መጓዝ እንደምንችል ያሳዩ ደማቅ ዐሻራዎች ናቸው።
በተለይም በቀን አንድ ጊዜ እንኳን መመገብ ለማይችሉ ዜጎች የተከፈቱት የተስፋ ብርሃን የምገባ ማዕከላት፣ እንዲሁም ተማሪዎችን በቀን ሁለት ጊዜ ተጠቃሚ ያደረገው ግዙፍ የትምህርት ቤት ምገባ ፕሮግራም፣ ትውልድን የመታደግ እና ማኅበራዊ ኃላፊነትን በላቀ ደረጃ የመወጣት ሕያው ማሳያዎች ናቸው።
በክረምት ወራትም የከተማዋ ነዋሪዎች ማዕድ በማጋራት እንዲሁም ዝቅተኛ ገቢ ያላቸውን ነዋሪዎች በልዩ ልዩ የሥራ ዕድሎች ተጠቃሚ በማድረግ የተሠራው ሥራ፣ የኅብር እና የመተጋገዝ ባህላችንን ጥልቀት በጉልህ ያመላክታል።
እነዚህ ተግባራት ዜጎችን ከረኃብ አደጋ መታደግ ብቻ ሳይሆን ለነገው ሀገር ተረካቢ ትውልድ አዕምሯዊ እና አካላዊ ብቃት ጠንካራ መሠረት የሚጥሉ ናቸው።
ተማሪዎች በባዶ ሆዳቸው ትምህርት ቤት ውለው ወደ ማቋረጥ እንዳያመሩ፣ እናቶችም የልጆቻቸውን ጉርስ በማሰብ ከሚደርስባቸው ከባድ የሥነ-ልቦና ጫና ነጻ እንዲሆኑ አስችሏል።
ከዚህም ባሻገር የከተማ ግብርናን በማስፋፋት የኑሮ ውድነቱን ጫና ለማቃለል የተወሰዱት ዕርምጃዎች የነዋሪውን ኑሮ በዘላቂነት ለመደገፍ ትልቅ አቅም ፈጥረዋል።
አዲስ አበባ እንደ ስሟ አበባ ልትሆን የምትችለው፣ ለነዋሪዎቿ ምቹ፣ ውብ እና ጽዱ ከተማ ሆና ስትገኝ ነው። የኅብር ቀን ይህንን የተጋመደ አንድነታችንን የምናሳይበት፣ ያጠራቀምነውን ማኅበራዊ ዕሴቶች ወደ ላቀ የልማት አቅም የምንቀይርበት ታሪካዊ ዕለት ነው።
ሀገርን የሚያሻግሩ እና የብልጽግና ትልሞችን ዕውን ለማድረግ የተጀመሩ ጥረቶች ከዳር ሊደርሱ የሚችሉት በአንድነት እና በኅብረት ስንተጋ ነው።
የቱሪስት መዳረሻነቷን ለማሳደግ የተገነቡት እንደ የወዳጅነት አደባባይ፣ የአንድነት ፓርክ፣ የእንጦጦ ፓርክ እና አዳዲስ የኮሪደር ልማቶች ከተማዋን እያዘመኗት ይገኛሉ።
በተጨማሪም የዓድዋ ድል መታሰቢያ፣ የሳይንስ ሙዚየም እና ዘመናዊ የትራንስፖርት ማዕከላት የከተማዋን ዕድገት የሚያፋጥኑ ሞተሮች ሆነዋል። ይህ ሁሉ የሚሆነው ግን ማኅበረሰቡን ባሳተፈ እና ዜጋን ማዕከል ባደረገ መልኩ ነው።
ዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ ያሉ ነዋሪዎችን ያቀፈው ይህ የኅብር ጉዞ፣ ብዝኃነት የኢትዮጵያ ጌጥ እና አቅም መሆኑን በተግባር እያረጋገጠ፣ ከተማዋን የሁሉም ዜጋ መኖሪያ እያደረጋት ይገኛል።
በበረከት ሽመልስ
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: