Search

ከአቧራማ ሜዳዎች እስከ ዘመናዊ ማዕከላት የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የስፖርት ዘርፍ ስኬት

ረቡዕ ጳጉሜን 04, 2018 27

በማንኛውም ሀገር የልማት ጉዞ ውስጥ የስፖርት መሠረተ ልማቶችን ማስፋፋት ብቁ እና አምራች ዜጋን ለመገንባት የሚደረግ ትልቅ ሀገራዊ ኢንቨስትመንት ነው።

በአዲስ አበባ ከተማ ባለፉት ጥቂት ዓመታት ከተከናወኑት ዐበይት የልማት ሥራዎች መካከል የመዲናዋን ወጣቶች እና የስፖርት ቤተሰብ የቆየ ጥያቄ የመለሱት የስፖርት ማዘውተሪያ ሥፍራዎች ግንባታ እና ማስፋፊያዎች በዋናነት ይጠቀሳሉ።

ቀደም ሲል የነበሩት ሜዳዎች አቧራማ እና በክረምት ወቅት ደግሞ የጭቃ ማከማቻ በመሆናቸው ስፖርተኞችን ለአካላዊ ጉዳት የሚያጋልጡ ነበሩ።

ዛሬ ላይ ግን በኮሪደር ልማት እና የወንዝ ዳርቻ ፕሮጀክቶች አማካኝነት ደረጃቸውን የጠበቁ ዘመናዊ ንጣፎች፣ ጥራት ያላቸው አጥሮች፣ የጽዳት እና አልባሳት መቀየሪያ ክፍሎች እንዲሁም በምሽት አገልግሎት የሚያስጡ የመብራት ዝርጋታዎች ተሟልተውላቸው አዲስ አየር እና ተስፋ ሰጪ መልክ አግኝተዋል።

ይህ ሰፊ የመሠረተ ልማት ዝርጋታ እንደ እግር ኳስ፣ አትሌቲክስ፣ የቅርጫት ኳስ፣ የመረብ ኳስ እና የእጅ ኳስ ካሉ የስፖርት ዓይነቶች ባሻገር እንደ ቴኳንዶ እና ስኬት ቦርድ ያሉ ዘርፎችም እንዲስፋፉ ምቹ አጋጣሚ ፈጥሯል።

 

በአሁኑ ወቅት በአዲስ አበባ በተገነቡት 2 ሺህ 580 በላይ የስፖርት ማዘውተሪያ እና ማሠልጠኛ ማዕከላት በሺዎች የሚቆጠሩ ታዳጊዎች የዕረፍት እና የክረምት ጊዜያቸውን በጥራት በተደራጁ ማዕከላት በማሳለፍ በሳይንሳዊ መልኩ እየሠለጠኑ ይገኛሉ።

በማዘውተሪያዎቹ በምሽት አገልግሎት መስጠት መጀመራቸው ነዋሪዎች ከሥራ በኋላ ተገናኝተው አካላዊ ብቃታቸውን እንዲያሳድጉ እና ማኅበራዊ ቁርኝታቸውን እንዲያጠናክሩም አስችሏል።

በትምህርት ቤቶች የሚገኙ መጫወቻ ሜዳዎችም ከትምህርት ሰዓት ውጭ ለአካባቢው ማኅበረሰብ ክፍት የሚሆኑበት አሠራር መዘረጋቱ የመሠረተ ልማቶችን ተዳራሽነት የበለጠ አጎልብቶታል።

እነዚህ ዐበይት የስፖርት መሠረተ ልማቶች ለተሰሩበት ዓላማ ብቻ እንዲውሉ ለማድረግ ጥበቃ እና ጥገናን ያካተተ አስተዳደራዊ ደንብ እና መመሪያ በማዘጋጀት ማዘውተሪያዎቹ ራሳቸውን በገቢ ማጠናከር የሚችሉበት አሠራር እና ለሌላ ልማት የሚነሱ ቦታዎች ምትክ የሚያገኙበት ሕጋዊ ሥርዓት ተዘርግቷል።

በመዲናዋ የተገነቡት አዳዲስ እና ነባር የስፖርት ማዘውተሪያዎች የከተማዋን ገጽታ ከመቀየር ባለፈ ብቁ፣ ጤናማ እና አምራች ዜጋን የማፍራት ጉዞውን እያፋጠኑት ይገኛሉ።

ይህንን ስኬት የበለጠ ለማስፋት እና የስፖርት ባህልን በመላ ከተማዋ ለማስረጽ፣ በሚቀጥሉት ጥቂት ዓመታት ውስጥ የከተማ አስተዳደሩ የመጫወቻና የስፖርት ማዘውተሪያ ስፍራዎችን ቁጥር ወደ 5 ሺህ ለማድረስ ዕቅድ ይዞ እየሠራ ነው።

በሰለሞን ገዳ

 

 

 

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: