የኅብር ቀን የብዝኃነታችንን ውበት የምናደምቅበት፣ የአብሮነታችንን መሠረት የምናድስበት እና በልዩነቶቻችን ውስጥ ያለውን የጋራ አቅም የምናጎለብትበት ታላቅ ዕለት ነው።
ኢትዮጵያ በብዙ ባህሎች፣ ቋንቋዎች እና አመለካከቶች የበለጸገች እንደመሆኗ መጠን፣ እነዚህን ጸጋዎች በአግባቡ ማስተናገድ እና ለጋራ ህልውና መጠቀም የጽናታችን መሰረት ነው።
ላለፉት ዘመናት ሲንከባለሉ የመጡ ውስብስብ የፖለቲካ፣ የማኅበራዊ እና የታሪክ ጥያቄዎችን በመነጋገር ለመፍታት የተጀመረው ሀገራዊ የምክክር ሂደት ይህንን የወል ትርክት የመገንባት እሴት በተግባር የሚያረጋግጥ ታሪካዊ ምዕራፍ ነው።
ልዩነትን ለፈጠሩ ጥያቄዎች ከግጭት ይልቅ ውይይትን መምረጥ የሰለጠነ ማኅበረሰብ መገለጫ ከመሆኑም ባሻገር ለዘላቂ ሰላም ብቸኛው አማራጭ ነው።
የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ሁሉንም የኅብረተሰብ ክፍል ያካተተ ሰፊ የአጀንዳ ማሰባሰብ ሥራ ያከናወነ ሲሆን 4 ሺህ የሁሉም ማኅበረሰብ ተወካዮች የተሳተፉበት ዋናው የምክክር ጉባኤ በስኬት ተጠናቅቋል።
በዚህ ታሪካዊ ጉባኤ በተደረጉ ጥልቅ እና አሳታፊ ውይይቶች በ99 በመቶ አጀንዳዎች ላይ ሙሉ መግባባት ላይ የተደረሰ ሲሆን፣ በቀጣይ ለሚወሰዱ እርምጃዎች የሚረዱ አቅጣጫ ጠቋሚ ምክረ ሀሳቦችም ተቀምጠዋል።
ተመካካሪዎቹ ስጋቶቻቸውን በነፃነት እያቀረቡ፣ የሌላውን ወገን ሀሳብ በትዕግሥት በማዳመጥ ያሳዩት ቁርጠኝነት፣ በሕዝባችን ዘንድ የነበረውን ጥንታዊ የመደማመጥ ባህል ወደ ዘመናዊ የፖለቲካ ምህዳር ያሸጋገረ ትልቅ እርምጃ ነው።
ይህም የሚያሳየው ዜጎች ልዩነቶቻቸው ምንም ያህል የሰፉ ቢመስሉም፣ በተቀራረበ እና በተከባበረ መንፈስ ከተወያዩ የመፍትሔ አቅጣጫዎችን የማግኘት ዴሞክራሲያዊ አቅም እንዳላቸው ነው።
በዚህ አሳታፊ ሂደት የተገኙትን ውጤቶች፣ የተደረሱ ዐበይት መግባባቶችን እና የተቀመጡ ምክረ ሀሳቦችን ወደ ተጨባጭ ሕጎች፣ ፖሊሲዎች እና ተቋማዊ ማሻሻያዎች መቀየር የቀጣዩ ምዕራፍ ዋና ተግባር ይሆናል።
የሂደቱ እውነተኛ ስኬት በሕዝቦች ዘንድ ዘላቂ ሰላም፣ መተማመን እና ጠንካራ ትስስር እንዲፈጠር በሚያደርገው አስተዋጽኦ የሚለካ ነው።
ከመከፋፈል ይልቅ መግባባትን፣ ከግጭት ይልቅ ምክክርን መምረጥ ለተረጋጋች እና ለበለጸገች ኢትዮጵያ ግንባታ ብቸኛው እና አስተማማኙ መንገድ ነው።
በኢንቲሃድ አብራር
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: