Search

ከባዶ የምሳ ዕቃ እስከ ብሩህ ተስፋ፤ የአዲስ አበባ ከተማ የተማሪዎች ምገባ መርሐ ግብር ስኬት

ረቡዕ ጳጉሜን 04, 2018 30

በመዲናችን የመንግሥት ትምህርት ቤቶች ግቢ ውስጥ የምሳ ደወል ሲደወል በረኃብ የተቆራመደ አንጀት እና በችግር ምክንያት የተሰበረ የመንፈስ ድካም የሚያንዣብብበት ጊዜ የቅርብ ጊዜ ትዝታ ነበር።

አዳጊዎች ከሰው ተደብቀው ወደ ዛፍ ጥላ ሥር የሚያመሩበት ባዶ የምሳ ዕቃ ይዘው በመምጣት ከማኅበራዊ የበታችነት ስሜት እና ከጓደኛ መገለል ለመዳን የሚጣጣሩበት እንዲሁም ከሰዓት በኋላ ባለው ክፍለ-ጊዜ በረኃብ ሳቢያ ተዝለፍልፈው ሲወድቁ ማየት የቀድሞው የከተማዋ ምሥል ነበር።

ይህንን ዘመናት የተሻገረ ማኅበራዊ ስቃይ እና የትውልድ ስብራት በዘላቂነት ለመቀየር በመደመር መንግሥት የተወጠነው የተማሪዎች ምገባ መርሐ ግብር፣ በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ተጨባጭ ለውጥ አምጥቷል።

2011 . 300 ሺህ ተማሪዎች የተጀመረው ይህ ጥረት አቅሙን በማሳደግ በአሁኑ ወቅት በቀን እስከ 1 ሚሊዮን የሚጠጉ የቅድመ-አንደኛ እና የአንደኛ ደረጃ ተማሪዎችን በቀን ሁለት ጊዜ ቁርስ እና ምሳ እንዲመገቡ ማድረግ አስችሏል።

በተጨማሪም 1 ነጥብ 1 ሚሊዮን በላይ ለሚሆኑ ተማሪዎች የትምህርት ቤት ደንብ ልብስ፣ ጫማ እና የመማሪያ ቁሳቁስ ድጋፍ ይደረጋል።

የከተማ አስተዳደሩ የጀመረው ይህ መርሐ ግብር በዓለም አቀፍ እና ቀጣናዊ የሳይንስ ጥናቶች የተረጋገጡ ማኅበራዊ ትሩፋቶችን በተግባር እያረጋገጠ ይገኛል።

 

የዓለም ምግብ ፕሮግራም (WFP) ከማስተር ካርድ ፋውንዴሽን ጋር ያጠናው ጥናት እንደሚያመላክተው፣ በትምህርት ቤት ምገባ ላይ በሚወጣ እያንዳንዷ 1 ዶላር 7 ነጥብ 2 ዶላር ዘላቂ የኢኮኖሚ ትርፍ ማስገኘት ይቻላል።

በአዲስ አበባ ኮልፌ ቀራኒዮ ክፍለ ከተማ የተደረገ ጥናት እንደሚያሳየው የምገባ መርሐ ግብሩ ከተዘረጋ በኋላ የተማሪዎች ትምህርት ማቋረጥ 3.18 ከመቶ ወደ 0.91 ከመቶ ዝቅ ብሏል።

ይህም በባንግላዴሽ፣ ታንዛኒያ እና ሩዋንዳ ከተደረጉ ጥናቶች ጋር የሚጣጣም ሲሆን የተማሪዎችን ተክለ ሰውነት እና ዕድገት ከማሻሻሉም በላይ 6 ክፍል 94 ከመቶ እና 8 ክፍል 88 ከመቶ ተማሪዎች ወደ ቀጣዩ ክፍል እንዲያልፉ ትልቅ አስተዋጽኦ አድርጓል።

በሌላ በኩል መርሐ ግብሩ ዝቅተኛ ገቢ ያላቸው ወላጆችን የኢኮኖሚ ሸክም በማቅለል 16 ሺህ በላይ አቅመ-ደካማ መጋቢ እናቶችን በማደራጀት ቋሚ የሥራ ዕድል መፍጠር ተችሏል።

አሠራሩን በዘመናዊ መልኩ ለመምራት "የተማሪዎች ምገባ ኤጀንሲ" ተቋቁሞ ጥብቅ የጥራት ቁጥጥር እየተደረገበት ይገኛል።

ይህ የአዲስ አበባ ተሞክሮ በዓለም አቀፍ ደረጃ ትልቅ ዕውቅና እና ሽልማት ያገኘ ለሌሎች አዳጊ ሀገራትም በአምሳያነት የሚጠቀስ ታላቅ ስኬት መሆን ችሏል።

ቀደም ሲል ይደርስ የነበረውን የሥነ-ልቦና ስብራት ጠግኖ በምትኩ በዕውቀት እና በራስ መተማመን የበለጸገ አዲስ ትውልድ እየተገነባ ይገኛ።

በሰለሞን ገዳ

 

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: