8.2 ትሪሊዮን ብር የሚያስተዳድር ተቋም! ይህ አሃዝ በዋዛ የሚታለፍ አይደለም፤ ይህን ግዙፍ ሀገራዊ ኃላፊነት ተሸክሞ በስኬት እየተራመደ የሚገኘው ተቋም ደግሞ የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግስ ነው።
በ2014ዓ.ም. የተቋቋመው ይህ ተቋም፣ በአጭር ጊዜ ውስጥ በአፍሪካ አህጉር ትልቁ የሉዓላዊ ሀብት ፈንድ ለመሆን በቅቷል።
የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግስ ከ40 በላይ ግዙፍ የመንግሥት የልማት ድርጅቶችን ስትራቴጂያዊ በሆነ መንገድ በስሩ አቅፎ በማስተዳደር የኢኮኖሚያችን አቅም ምን ያህል ሰፊ እንደሆነ በተግባር እያሳየ ይገኛል።
ብሔራዊ የልማት እና የንግድ ሀብቶችን በማዕከላዊ የካፒታል አስተዳደር ስር ማሰባሰብና በዘመናዊ የኮርፖሬት አሠራር መምራት የተቋቋመበት ዋንኛ ዓላማው ነው።
ከዚህም ባለፈ ሀብትን በማስፋፋት፣ የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንትን በመሳብ እና ከዓለም አቀፍ ኩባንያዎች ጋር በትብብር በመሥራት ለአሁኑም ሆነ ለመጪው ትውልድ የሚሻገር ዘላቂ እሴት መፍጠርን ግቡ አድርጓል።
ይህ ዘመናዊ አሠራር የመንግሥት ልማት ድርጅቶችን ከዚህ ቀደም ይገጥማቸው ከነበረው የዕዳ፣ የአሠራር ድክመት እና የኪሳራ ጫና በማውጣት የብሔራዊ ኢኮኖሚው ዋና ሞተር እንዲሆኑ አስችሏል።
ተቋሙ በአጭር ጊዜ ውስጥ ያስመዘገባቸው አሃዛዊ ስኬቶች የሄደበትን ርቀት በግልጽ ያሳያሉ። በተጠናቀቀው የበጀት ዓመት ብቻ 3.06 ትሪሊዮን ብር አጠቃላይ ገቢ ማስገኘት የቻለ ሲሆን፣ ከዚህም ውስጥ 475 ቢሊዮን ብር ከታክስ በፊት ትርፍ አግኝቷል።
ለሀገራዊ አጠቃላይ የታክስ ገቢ 17.7 በመቶ ሽፋን በመስጠት 378 ቢሊዮን ብር ታክስ ወደ መንግሥት ካዝና ገቢ አድርጓል።
ከገቢ እና ትርፍ ባሻገርም ከ180 ሺህ በላይ ለሚሆኑ ዜጎች አዳዲስ የሥራ ዕድሎችን በመፍጠር ማኅበራዊ ኃላፊነቱን በከፍተኛ ደረጃ እየተወጣ ይገኛል።
የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግስ ስኬት በፋይናንስ አሃዝ ብቻ የሚገለጽ አይደለም። ከኢትዮ ቴሌኮም እስከ ኢትዮጵያ አየር መንገድ፤ ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ እስከ ኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ያሉ ዐበይት ብሔራዊ ተቋማትን በማስተባበር እና የማስፈጸም አቅማቸውን በማሳደግ ረገድ ትልቅ ሚና እየተጫወተ ነው።
አሁን ደግሞ አድማሱን በማስፋት የመንግሥት የልማት ድርጅቶችን በኢትዮጵያ ሰነደ ሙዓለ ንዋይ ገበያ ላይ በማሳተፍ ብሎም ከዓለም አቀፍ ባለሀብቶች ጋር በጋራ በመሥራት የኢንቨስትመንት አቅምን ወደ አዲስ ምዕራፍ እያሸጋገረ ነው።
ይህ ስኬታማ ጉዞ የሕዝብ ንብረት የሆኑ ተቋማት የዛሬ የዕለት ደጋፊዎች ብቻ ሳይሆኑ፣ የነገም አስተማማኝ የትውልድ ሀብት መሆናቸውን በተግባር የሚያረጋግጥ ብሩህ እርምጃ ነው።
በለሚ ታደሰ
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: