Search

የጋራ መግባባት ዴሞክራሲ በተግባር፡ የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ጉዞ

ማክሰኞ መስከረም 05, 2019 101

የመግባባት ዴሞክራሲ ጽንሰ-ሐሳብ በወረቀት ላይ ከሚሰፍር እና በቃላት ከሚገለጽ መርህ አልፎ በተግባር ሲተረጎም በኢትዮጵያ የተካሄደው ሀገራዊ የምክክር ሂደት ለዚህ ህያው ማሳያ ነው።

የብዝኃ ማንነት፣ ባህል እና የተለያዩ የፖለቲካ ዕይታዎች መገኛ የሆነችው ኢትዮጵያ ዘላቂ ሰላሟን እና ኅብረ-ብሔራዊ አንድነቷን ለማረጋገጥ ይህ አካሄድ ወሳኝ መሆኑን በተግባር እያስመሰከረች ትገኛለች።

ይህን መርህ ወደ ላቀ ደረጃ በማሸጋገር ረገድ የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ትልቁን የታሪክ ድርሻ ይወስዳል።

ኮሚሽኑ የአጀንዳ ማሰባሰብ ተግባራትን 93 በመቶ በላይ በሚሆኑ የኢትዮጵያ ክፍሎች በስኬት በማከናወን፣ እንዲሁም 4 ሺህ ተወካዮች የተሳተፉበትን ዋና ጉባኤ በማጠናቀቅ ቁልፍ ምክረ-ሀሳቦችን በብቃት አሰባስቧል።

ሀገራዊ ምክክሩ የመግባባት ዴሞክራሲ መገለጫ መሆኑን ከተረጋገጠበት መዋቅራዊ ምክንያት አንዱ የሂደቱ ሙሉ አሳታፊነት እና ከታች እስከ ላይ የተዘረጋው አካታችነቱ ነው።

በምክክር ሂደቱ ከወረዳ እስከ ማዕከል ከተለያዩ የማኅበረሰብ ክፍሎች፣ ከፖለቲካ ኃይሎች፣ ከሃይማኖት አባቶች፣ ከሲቪክ ማኅበራት፣ ከወጣቶች፣ ከሴቶች እና ከተፅዕኖ ፈጣሪ ግለሰቦች የተወጣጡ በርካታ ተወካዮች በነፃነት ሐሳባቸውን አንሸራሽረዋል።

ይህ ሰፊ ተሳትፎ ማናቸውም ሀገራዊ ውሳኔዎች በጥቂቶች ፍላጎት ወይም በአብላጫ ድምፅ ጫና ብቻ ሳይሆን በሁሉ አቀፍ ውይይት እና በጋራ መግባባት እንዲቃኙ በማድረግ ዴሞክራሲያዊ እሴትን ገንብቷል።

የምክክር መድረኩ ዋነኛ ስኬት የኢትዮጵያን ፖለቲካ ከአሸናፊ እና ተሸናፊ ሥነ-ልቦና ማውጣት መቻሉ ነው።

በልማደኛው የፖለቲካ ውድድር አንዱ ወገን አሸናፊ ሌላው ተሸናፊ ሆኖ ሲወጣ ሀገራዊ ምክክሩ ግን ጠረጴዛ ዙሪያ በመቀመጥ ሁሉንም አካላት አሸናፊ የሚያደርግ የጋራ መፍትሔ ማፈላለጊያ መድረክ ሆኗል።

ለዘመናት ሲንከባለሉ የመጡ መዋቅራዊ ውዝግቦችን፣ የታሪክ ስብራቶችን እና የተንሰራፉ ልዩነቶችን በሰከነ ውይይት ለመፍታት የተዘረጋው መንገድ፤ የመግባባት ዴሞክራሲ ለኢትዮጵያ ያለውን ሁለንተናዊ ፋይዳ በግልጽ ያሳያል።

ከተለመደው የፖለቲካ ንትርክ ወጥቶ በመረጃ እና በምክንያት ላይ የተመሰረተ የውይይት ባህልን ማዳበሩም የሂደቱ ሌላኛው ትሩፋት ነው።

በዚህም በስኬት የተካሄደው ይህ ሀገራዊ የምክክር ሂደት የመግባባት ዴሞክራሲን ባህል በኢትዮጵያ የፖለቲካ ምህዳር ውስጥ በጥንካሬ ለማስረጽ እና ዘላቂ ሰላምን ለማረጋገጥ የሚያስችል ጠንካራ መሠረት ጥሏል።

አሁን የሚቀረው ትልቁ የቤት ሥራ በዋናው ጉባኤ የተሰባሰቡት ምክረ-ሀሳቦች እና የጋራ መግባባቶች በሚመለከታቸው አካላት አማካኝነት ወደ መሬት ወርደው በተግባር ሲተረጎሙ ማየት ነው።

ይህ ሲሆን ልዩነቶቻችን የውበት እና የጥንካሬያችን ምንጭ የሚሆኑባት ዘመናዊት ኢትዮጵያ እውን ትሆናለች።

በሔዋን ጌታቸው

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: