የተነቃቃው የማዕድን ዘርፍ ለጸናች ሀገር ግንባታ!
(የዕለቱ መልዕክት)
በአንድን ሀገር የምርት ማሳለጫ ከሚባሉና ጠንካራ ኢኮኖሚ ከሚገነቡ መሠረታዊ ሀብቶች ውስጥ ዋነኛው መሬትና በውስጡ ያዘለው የተፈጥሮ ጸጋ ነው።
ሀገራችን ኢትዮጵያ ከጥንታዊ ሥልጣኔዋ ጀምሮ በከርሰ ምድሯ ያቀፈችው እምቅ የማዕድን ሀብት ቢኖራትም፣ ይህ ሀብት ለዘመናት የጎላ የኢኮኖሚ እሴት ሳይፈጥር መቆየቱ የሁላችንም የቁጭት ምንጭ ሆኖ አልፏል።
ሆኖም በቅርብ ዓመታት የመደመር መንግሥት የማዕድን ዘርፉን የኢኮኖሚው አንዱ ምሶሶ በማድረግ፣ የጸናችና የኢኮኖሚ ሉዓላዊነቷ የተረጋገጠ ሀገር ለመገንባት በሰጠው ልዩ ትኩረት፤ ኢትዮጵያ ከአፈር በታች ያለውን ሀብቷን ወደ እውነተኛ ብልጽግና እና የቴክኖሎጂ ሽግግር እየቀየረች ትገኛለች።
በኮንትሮባንድና በተደራጀ ሕገ-ወጥ አሠራር ምክንያት ለረጅም ጊዜ በጥቂቶች መጠቀሚያነት ብቻ ተወስኖ የቆየው የማዕድን ዘርፍ፣ በማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያው አማካኝነት በቴክኖሎጂ እንዲታገዝና ተጠያቂነት እንዲሰፍንበት ተደርጓል።
ለዚህ ሪፎርም ተጨባጭ ማሳያ የሆነው የወርቅ ገበያ ነው። የግብይት ሥርዓቱ በመዘመኑ ብቻ የወርቅ ምርት በ2012 ዓ.ም ከነበረበት 3.3 ቶን ምርት፣ በ2017 ዓ.ም ወደ 38.83 ቶን ከፍ ማለት ችሏል።
ቀድሞ በመቶ ሚሊዮኖች ብቻ ይገኝ የነበረው የውጭ ምንዛሬ ገቢም በዚያው ልክ በማደግ በቢሊዮኖች የሚቆጠር ዶላር ማስገኘት መቻሉ፣ የዘርፉን አቅም ከማሳየት ባለፈ ለሀገር አቀፍ የውጭ ምንዛሬ ክምችት ትልቅ አቅም ፈጥሯል።
የኩርሙክ፣ የቱሉ ካፒ፣ የሚድሮክ መተከልና የኤትኖ ማይኒንግ ግዙፍ ፕሮጀክቶችም ይህን እመርታ ይበልጥ እያጸኑት ይገኛሉ።
የዛሬው ርምጃችን ማዕድንን እንዳለ በጥሬው ወደ ውጭ ከመላክ ልማድ የወጣ ነው። እንዲህ ያለው በጥሬ ምርት ላይ እሴት በመጨመር የገቢ ምርቶችን የመተካት አሠራር ራሷን የቻለችና የጸናች ሀገርን ለመገንባት ትልቅ መሠረት ነው።
በዓመት ከ300 ሚሊዮን ዶላር በላይ የውጭ ምንዛሬ ይወጣበት የነበረው የድንጋይ ከሰል በአዳዲስ የሀገር ውስጥ ፋብሪካዎች ሙሉ በሙሉ መተካት መቻሉም ሌላው ትልቅ ስኬት ነው።
በተጨማሪም ለሚ ናሽናል ሲሚንቶን ጨምሮ አዳዲስ ግዙፍ አምራቾች ወደ ገበያ በመቀላቀላቸው፣ የሲሚንቶ አቅርቦታችን ከ9.1 ሚሊዮን ቶን በላይ ከፍ ብሏል።
በግንባታና ሴራሚክስ ዘርፍም የባይጂያ እና የግራንዴር ፋብሪካዎች ኢንዱስትሪውን በማዘመን ላይ መሆናቸው የኢኮኖሚ ሉዓላዊነታችን ማረጋገጫዎች ናቸው።
በሶማሌ ክልል የካሉብ የፈሳሽ ነዳጅ ፕሮጀክት፣ የጋዝ ቧንቧ መስመር መዘርጋት፣ የኃይል ማመንጫ ግንባታ፣ እንዲሁም ለግብርናው ዘርፍ ወሳኝ የሆነው የዩሪያ ማዳበሪያ ፕሮጀክት የማዕድን ዘርፉን ከሌሎች የኢኮኖሚ ምሶሶዎች ጋር በማስተሳሰር ለሀገር ሁለንተናዊ ልማት ከፍተኛ አስተዋጽኦ እያበረከቱ ነው።
ሀገር በቀል አቅምን ይበልጥ ለማሳደግም እንደ ሊቲየምና ታንታለም ባሉ ዓለም አቀፍ ተፈላጊነት ባላቸው ስትራቴጂያዊ ማዕድናት ላይ ሰፊ ጥናት እየተደረገ መሆኑ የነገዋን የበለጸገች ኢትዮጵያ ብሩህ ተስፋ ያሳያል።
እነዚህ ሁሉ ስኬቶች ትርጉም የሚኖራቸውና ዘላቂ የሚሆኑት ማኅበረሰቡ በቀጥታ የልማቱ ተጠቃሚ መሆን ሲችል ነው። ስለሆነም አሁን ላይ ማዕድን በሚወጣባቸው አካባቢዎች የሚኖረው ማኅበረሰብ በሮያሊቲ ክፍያና ታክስ ተጠቃሚ እንዲሆንና ማኅበራዊ መሠረተ ልማቶች እንዲስፋፉ የተፈጥሮ ሚዛንን በማይጎዳ መልኩ ጥብቅ የቁጥጥር ሥርዓት ተዘርግቶ እየተሠራ መሆኑ እጅግ የሚበረታታ ነው።
በአጠቃላይ የማዕድን ዘርፉ ከሕገ-ወጥነት ጸድቶ የተፈጥሮ ሀብትን በዕውቀትና በቴክኖሎጂ በማዋሃድ ኢኮኖሚያዊ መሰረቷ የጸና፣ ሉዓላዊነቷ የተከበረና ዜጎቿ የበለጸጉባት ጠንካራ ሀገር ለመገንባት በሚደረገው ጉዞ ውስጥ የጀርባ አጥንት መሆኑን በተግባር እያሳየ ነው።
ይህ የተጀመረው በራስ አቅም የመቆም እውነተኛ የብልጽግና ጉዞ ተጠናክሮ ሊቀጥል ይገባዋል።
የኢቢሲ ዶትስትሪም ኤዲቶሪያል
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: