"ጊፋታ" ከባህላዊ የዘመን መለወጫነት እስከ ማኅበራዊ የኢኮኖሚ ሕዳሴ የዘለቀ የቁጠባ እና የአብሮነት ጥበብ ነው፡፡
በዓሉ በተባበሩት መንግሥታት የትምህርት፣ የሳይንስና የባህል ድርጅት (ዩኔስኮ) የማይዳሰስ የዓለም ቅርስ ሆኖ የተመዘገበ የወላይታ ብሔር ለዓለም ያበረከተው ድንቅ ስጦታ ነው፡፡
ጊፋታ የወላይታ ብሔር ተወላጆች የጨረቃን ዑደት በማስላት ከክረምት ወደ በጋ፣ ከጭጋጋማ ድባብ ወደ ብርሃናማ ዓውድ፣ ከአሮጌው ዓመት ወደ አዲስ ዓመት የሚሸጋገሩበትና በታላቅ ድምቀት የሚያከብሩት የዘመን መለወጫ በዓል ነው፡፡
በብሔሩ ዘንድ ትልቅ ቦታ የሚሰጠው ሲሆን፣ "ጊፋታ" የሚለው ቃልም ታላቅ፣ የመጀመሪያ ወይም ባይራ (በኩር) የሚል ትርጉም አለው፡፡
በዓሉ በውስጡ በርካታ ባህላዊ፣ ታሪካዊ፣ የሚዳሰሱ እና የማይዳሰሱ እሴቶችን አቅፎ ይዟል፡፡ ለአብነትም አብሮነት፣ ታላላቆችን ማክበር፣ ተስፋ መሰነቅ፣ ባህልን ማስተዋወቅ፣ መከባበር፣ ዕርቅ፣ አብሮ መዝናናት፣ መረዳዳት፣ ቁጠባና ምስጋና ከዋና ዋናዎቹ እሴቶች መካከል ይጠቀሳሉ፡፡
ቁጠባ የጊፋታን እሴት ከማጠናከር በተጨማሪ የኅብረተሰቡን የኢኮኖሚ አቅም ያጎለብታል፡፡ በበዓሉ ሰሞን የሚከናወነው የቁጠባ ባህል ከልጅ እስከ ወላጅ ሙሉ የማኅበረሰብ ክፍሎችን የሚያሳትፍ በመሆኑ፣ የተረጋጋ የቤተሰብና የማኅበረሰብ ኢኮኖሚ እንዲኖር ያለው ፋይዳ ከፍተኛ ነው፡፡
በየዓመቱ "ሹሃ ዎጋ" በሚባለው እና በእርጥብ ቆዳ ላይ በሚጀመረው የቁጠባ ሥርዓት፣ አባቶች ለሰንጋ በሬ መግዣ የሚያደርጉት ቁጠባ ለመጪው ጊፋታ ከበሬ መግዣ አልፎ ለተለያዩ ማኅበራዊ ጉዳዮች ይውላል፡፡
በዚህም አባቶች በበዓል እና ከበዓል ጋር ተያይዘው በሚመጡ ወጪዎች ሳይቸገሩ በዓሉን ያሳልፋሉ፡፡
እናቶች የሚያደርጉት የቅቤ ዕቁብ ደግሞ የኢኮኖሚ አቅማቸውን ከማጎልበት አልፎ እርስ በርስ የመተሳሰብ እሴታቸውን ያጠናክራል፡፡
በዕቁቡ ሂደት ውስጥ የአንዷ አቅም ቢዳከም ወይም ችግር ቢገጥማት፣ ሌሎች እናቶች በመተሳሰብና በመረዳዳት አስፈላጊውን ድጋፍ ያደርጉላታል፡፡
ልጆች ከወላጆቻቸውና ከቅርብ ዘመዶቻቸው የሚያገኙትን ገንዘብ ለጊፋታ አዲስ ልብስ ለመግዛት ይቆጥባሉ፡፡
ይህም ልብስ ከመግዛት አልፎ ከበዓሉ ማግስት ለሚጀመረው የትምህርት ዘመን የሚያስፈልጓቸውን ቁሳቁሶች ለመግዛት ይረዳቸዋል፡፡
ሴት ወጣቶችም በተመሳሳይ ለአልባሳትና ለጌጣጌጥ የሚያደርጉት ቁጠባ የዚሁ በዓል ድንቅ እሴት አካል ነው፡፡
በወላይታ ብሔር ለጊፋታ የሚደረገው የቁጠባ ባህል ኅብረተሰቡ ሀብቱን በአግባቡ እና በጥንቃቄ እንዲጠቀም ያደርጋል፡፡
ከቁጠባ ባሻገር የዕርቅ፣ የተስፋ፣ የመልካም ምኞት፣ የምስጋና፣ ልዩ የገበያ፣ የአልባሳት እና የአመጋገብ ሥርዓቶችን ያቀፈው ይህ በዓል፣ ካለው ከፍተኛ ማኅበራዊ እና ባህላዊ ፋይዳ የተነሣ በዩኔስኮ የማይዳሰስ የዓለም ቅርስ ሆኖ ተመዝግቧል፡፡
ታዲያ ይህ የባለብዙ እሴቶች ሀብት የሆነው የወላይታ ብሔር የዘመን መለወጫ በዓል "ጊፋታ" መስከረም 10/2019 ዓ.ም በድምቀት ይከበራል፡፡
በትዕግስቱ ቡቼ
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: