Search

የጸጥታ ተቋማት ሪፎርም፡ ሉዓላዊነትን ከመጠበቅ እስከ የዜጎችን ደኅንነት ማረጋገጥ

ረቡዕ መስከረም 06, 2019 64

የአንድ ሀገር ሉዓላዊነት፣ ሰላምና የዜጎች ደኅንነት በጠንካራ የጸጥታ ተቋም ላይ የተመሠረቱ ናቸው። የዘመኑ የጸጥታ ምህዳር ግን ቀድሞ ከነበረው በእጅጉ ተለውጧል። ዛሬ ሀገራት ከባህላዊ የደኅንነት ስጋቶች በተጨማሪ ሳይበር ጥቃት፣ የተደራጀ ወንጀል፣ ሕገወጥ የሰዎች ዝውውርና ሌሎች ድንበር ተሻጋሪ ስጋቶችን መቋቋም ይጠበቅባቸዋል።

ይህ ሁኔታ የጸጥታ ተቋማት የሚሠሩበትን መንገድ እንዲቀይሩ አስገድዷቸዋል። በኢትዮጵያም በቅርብ ዓመታት የተካሄዱ የጸጥታ ዘርፍ ሪፎርሞች ተቋማትን በአደረጃጀት፣ በሰው ኃይል፣ በቴክኖሎጂ፣ በመሠረተ ልማትና በአሠራር ለማዘመን ያተኮሩ ናቸው።

የጸጥታ ተቋማት ተልዕኮ የሀገርን ሉዓላዊነትና ሕገመንግሥታዊ ሥርዓት ከመጠብቅ ባሻገር የሕዝብን ሰላምና ደኅንነት ማረጋገጥ፣ ወንጀልን መከላከልና ሕግ ማስከበርን ያካትታል።

በዘመናዊ የጸጥታ አሠራር ውስጥ ደግሞ ተቋም አደጋ ከተፈጠረ በኋላ ብቻ ምላሽ የሚሰጥ ሳይሆን ስጋቶችን ቀድሞ መለየት፣ መተንበይና መከላከል የሚችል አቅም መገንባት ይጠበቅበታል። በዚህ ረገድ የመረጃ አቅም፣ የምርመራ ብቃት፣ የቴክኖሎጂ አጠቃቀምና ተቋማዊ ቅንጅት ወሳኝ ናቸው።

በተለይ የፌዴራል ፖሊስ የፎረንሲክ ሳይንስ አቅምን ማሳደጉ የወንጀል ምርመራን ከግምትና ከግል ግንዛቤ ወደ ሳይንሳዊ ማስረጃ ለማሸጋገር የሚያግዝ ለውጥ ነው። የፌዴራል ፖሊስ የፎረንሲክ ምርመራ የምርመራ ቴክኒኮችን ጨምሮ ዘመናዊ አቅምን እንድገነባ ትልቅ አስተዋጽዖ አበርክቷል።

የጸጥታ ምህዳሩ ወደ ዲጂታል ዓለም በመስፋፋቱ የሳይበር ደኅንነት የብሔራዊ ደኅንነት ዋና አካል ሆኗል። የኢትዮጵያ ብሔራዊ የሳይበር ደኅንነት ፖሊሲም ዲጂታል ለውጥ ከሚያመጣቸው ዕድሎች ጎን ለጎን በዜጎች፣ በመረጃዎችና በወሳኝ መሠረተ ልማቶች ላይ የሚደርሱ የሳይበር ስጋቶችን መቋቋም አስፈላጊ መሆኑን ያስቀምጣል።

ዘመናዊ መሣሪያ መግዛት ብቻ የጸጥታ ተቋምን ዘመናዊ አያደርገውም። ቴክኖሎጂውን በብቃት የሚጠቀም፣ መረጃን የሚተነትን፣ ሕግንና የሰብዓዊ መብት መርሆዎችን የሚያከብር የሰው ኃይል ከመሣሪያው እኩል ወሳኝ ነው።

በዚህም የፖሊስ ምርምርና ስልጠና ተቋማት የግጭት አመራር፣ የሰላም ግንባታ፣ ድንበር ተሻጋሪ ወንጀሎችና ሕገ ወጥ የሰዎች ዝውውር ያሉ ዘርፎችን በምርምር መዳሰሳቸው የሙያዊ አቅም ግንባታው አካል ነው።

የጸጥታ ተቋማት ሪፎርም በአንድ ጊዜ ተከናውኖ የሚያበቃ ሂደት አይደለም። የስጋቶች ባህሪ በየጊዜው ስለሚለዋወጥ ተቋማትም በተመሳሳይ ፍጥነት መማር፣ መላመድና መታደስ ይኖርባቸዋል።

በመሆኑም የኢትዮጵያ የጸጥታ ተቋማት ሽግግር ከባህላዊ የጸጥታ አሠራር ወደ ተቋማዊ አደረጃጀት፣ ሳይንሳዊ ምርመራ፣ ዲጂታል አቅም፣ የሰው ኃይል ግንባታና የተቀናጀ የጸጥታ አሠራር የሚያመራ ሂደት ነው። የዚህ ሽግግር ዋና ግብም ቴክኖሎጂን ለመጠቀም ብቻ ሳይሆን የሀገርን ሉዓላዊነት በማስጠበቅ፣ ሕግን በማስከበር እና የሕዝብን ሰላምና ደኅንነት በዘላቂነት ማረጋገጥ ነው።

 

በአድማሱ አራጋው

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: