Search

ኮፕ 32 በታላቁ ሩጫ

ሓሙስ ጥቅምት 26, 2019 57

የወጣቶችና ስፖርት ሚኒስቴር እና "ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ"፣ ሀገራችን የምታዘጋጀውን የዓለም አየር ንብረት ለውጥ ጉባኤ (ኮፕ 32) አስቀድሞ ኢትዮጵያን የስፖርት መዳረሻ አድርጎ ለማስተዋወቅና የስፖርትን ሁለንተናዊ አቅም ለመጠቀም የሚያስችል የመግባቢያ ስምምነት ተፈራረሙ።

በስምምነቱ ወቅት የወጣቶችና ስፖርት ሚኒስትር አክሊሉ ታደሰ (ዶ/ር) እንደገለጹት፤ ስፖርት የዜጎችን ጤና፣ ሰላምና መቀራረብ የሚያጠናክር በመሆኑ እንደ ታላቁ ሩጫ ያሉ ሀገራዊ ሀብቶችን በመጠቀም የመንግሥትን የዘርፍ ግቦች ማሳካት አስፈላጊ ነው።

በተጨማሪም ስምምነቱ ኢትዮጵያ ለኮፕ 32 ጉባኤ በምታደርገው ዝግጅት ስፖርትን እንደ ዋና መድረክ ለመጠቀም፣ ሀገራዊ እንቅስቃሴዎችን ከዓለም አቀፍ ተሳትፎ ጋር ለማቀናጀትና ለወጣቶች ዕድገት እንዲሁም ለኢኮኖሚ መነቃቃት ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንደሚያበረክት አመላክተዋል።

የስፖርት ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ መኪዩ መሐመድ በበኩላቸው፤ ስምምነቱ በየደረጃው ለሚከናወኑ የስፖርት መድረኮች አቅም በመሆን፣ የማህበረሰብ ተሳትፎን ለማሳደግ፣ የህዝብ ለህዝብ ወዳጅነትን ለማጠናከር እንዲሁም የስፖርት ቱሪዝምና ዲፕሎማሲን ለማስፋፋት ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያበረክታል ሲሉ ገልጸዋል።

የታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ ዋና ሥራ አስኪያጅ ወጣት ዳግማዊት አማረ እንደገለጹት፤ የታላቁ ሩጫ ዋና ግብ ስፖርቱን በመላ በሀገራችን ማስፋፋት በመሆኑ፣ የተደረገው ስምምነት በየደረጃው ከሚካሄዱ የማህበረሰብ ተሳትፎ መድረኮች ጋር ተቀናጅቶ ለመስራት ትልቅ አቅም ይፈጥራል።

ይህ የመግባቢያ ስምምነት የታላቁ ሩጫ ዋና ዋና የስፖርት መድረኮችን፣ በተለይም የ10 ኪሎ ሜትር ውድድርንና የ"ልወቅሽ ኢትዮጵያ" ዝግጅቶችን በመጠቀም ኮፕ 32ን ወደ ማህበረሰቡ ለማቅረብና ስፖርትን ባህሉ ያደረገ ማህበረሰብ ለመፍጠር የሚያስችል መሆኑን የባህልና ስፖርት ሚኒስቴር መረጃ ያመላክታል።

በሌላ በኩል የዘንድሮው የማስ ስፖርትና "ስፖርት ለሁሉ" ፕሮጀክት በአዲስ አበባ፣ በአርባ ምንጭ፣ በቦቆጂ፣ በጂማ፣ በደብረ ብርሃን እና በሐረር ከተሞች ደረጃውን ጠብቆ እንደሚካሄድ ተገልጿል።

 

በዚህም መሠረት ከ80 ሺህ በላይ የሀገር ውስጥ እና የውጭ ሀገር ታዳሚያን የሚሳተፉበት፣ ኮፕ 32 ጉባኤን ለማስተዋወቅ እና ፍቅር፣ ሰላም እና ጤና የሚሰበክበት የአዲስ አበባው ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ በአዲስ አበባ ይካሄዳል።

 

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: