Search

የሁለተኛው ትውልድ የአርበኝነት ጥሪ፣ የኢትዮጵያ የታሪክ አደራ፣ የባሕር በር ተፈጥሯዊ መብት እና የጠላቶች ሴራ ማምከኛ አንድነት

ቅዳሜ መስከረም 23, 2019 114

ኢትዮጵያ ከ130 ሚሊዮን በላይ ሕዝብ ያላት፣ በሕዝብ ብዛት ከአፍሪካ ሁለተኛ እንዲሁም በዓለም ላይ ካሉ የባሕር በር የሌላቸው ሀገራት መካከል ደግሞ ቀዳሚዋ ናት።

የሀገር ዕድገትና የሕዝብ ቁጥር መስፋፋት ከተፈጥሮ ሀብት አጠቃቀምና ከንግድ መስመሮች ጋር ቀጥተኛ ቁርኝት ያለው ሲሆን፣ ኢትዮጵያ ከቀይ ባሕርና ከኤደን ባሕረ ሰላጤ ጋር ያላት ቁርኝት ትናንት የተጀመረ ሳይሆን የረጅም ዘመናት የታሪክ እውነት ነው።

በአክሱም ሥልጣኔ ወቅት አዱሊስ በመባል ይታወቅ የነበረው የቀይ ባሕር ወደብ ለአክሱም ንግድ፣ የባሕር ኃይልና ከሩቅ ምስራቅ እስከ ሜዲትራኒያን ከነበሩት ዓለም አቀፍ ማህበረሰቦች ጋር ለመገናኘት ዋና በር ነበር።

ሆኖም በተለያዩ ታሪካዊ አጋጣሚዎች፣ ጂኦፖለቲካዊ ለውጦችና በ1980ዎቹ መጨረሻ በታዩ ፖለቲካዊ ክስተቶች ምክንያት ኢትዮጵያ የባሕር በሯን እንድታጣ ሆነች። ይህ የባሕር በር ማጣት የሀገራችንን የታሪክ ጉዞ፣ የንግድ መስመርና የደኅንነት መዋቅር በእጅጉ የጎዳ የታሪክ ጠባሳ መሆኑ የብዙዎች ስምምነት ነው።

በአሁኑ ወቅት የቀይ ባሕርና የኤደን ባሕረ ሰላጤ ቀጣና በዓለም አቀፍ የንግድና የደኅንነት መዋቅር ውስጥ እጅግ ወሳኝ ስትራቴጂካዊ ቦታ አላቸው።

የአሜሪካ፣ የቻይና፣ የአውሮፓ ሀገራትና የባሕረ ሰላጤው ሀገራት በዚህ ቀጣና ያላቸው የጦር ሰፈርና ወታደራዊ እንቅስቃሴ የቀጣናውን ከፍተኛ አስፈላጊነት ያሳያል።

በምስራቅ አፍሪካ ትልቋና የኃይል ማዕከል የሆነች ሀገራችን ኢትዮጵያ፣ በዚህ ወሳኝ የውኃ አካል ላይ ቀጥተኛ መግቢያና ተጽዕኖ እንዳይኖራት መደረጉ የቀጣናውን የኃይል ሚዛንና ዘላቂ ሰላም የሚፈታተን ነው።

የባሕር በር አለመኖር ለኢትዮጵያ በቀላሉ የሚታይ ሳይሆን በየቀኑ የሚከፈል ከፍተኛ የኢኮኖሚ ዋጋ ነው። ሀገራችን በየዓመቱ በቢሊዮን የሚቆጠሩ ዶላሮችን ወደብ ኪራይ ክፍያ ታወጣለች።

በዚህም የትራንስፖርትና የሎጂስቲክስ ወጪ ከፍተኛ በመሆኑ የኢትዮጵያ ምርቶች በዓለም አቀፍ ገበያ ተወዳዳሪ እንዳይሆኑ ያደርጋል፤ የጥሬ ዕቃዎች በፍጥነት አለመድረስና የወደብ መጨናነቅ የኢንዱስትሪ ፓርኮችንና የአምራች ዘርፉን ምርታማነት ይገድባል።

የባሕር በር ተፈጥሯዊ መብታችንን ለማረጋገጥ የምናደርገው ጉዞ እና የግብፅና የሻዕቢያን እኩይ ሴራ ማምከን፣ የዚህ ትውልድ የሁለተኛው ትውልድ አርበኝነት ዋነኛ አጀንዳ ነው።

ታሪካዊ ጠላቶቻችን ኢትዮጵያን ለማዳከም፣ በኢኮኖሚ አረንቋ ውስጥ ለማስቀረት እና የቀጣናው ሀይል ሆና እንዳትወጣ ሌሊትና ቀን በሴራ ሲደክሙ ይኖራሉ።

ይህንን የተደቀነብንን አደጋ ለማክሸፍ መላው የኢትዮጵያ ህዝብ ውስጣዊ ልዩነቶቹን ወደ ጎን በመተው እንደ አንድ ልብ መካሪ፣ እንደ አንድ ቃል ተናጋሪ ሆኖ ከሀገሩ ጎን ሊቆም ይገባል።

የኢትዮጵያ የባሕር በር ጥያቄ ከጎረቤት ሀገራት ጋር የሚደረግ የጉልበት ወይም የኃይል አማራጭ ሳይሆን፣ በሕጋዊና ሰላማዊ መንገድ የጋራ እድገትን ማዕከል ያደረገ ነው።

ኢትዮጵያ ያላትን ሰፊ የሕዝብ ቁጥር፣ የታዳሽ ኃይል፣ የግብርና ምርቶችና የትራንስፖርት መሠረተ ልማት ከጎረቤት ሀገራት የወደብ ሀብት ጋር በማጣመር የጋራ ብልጽግናን መፍጠር ይቻላል።

በምስራቅ አፍሪካ በነፃ የንግድ ቀጣና እና በቀጣናዊ ትስስር በኩል የኢኮኖሚ ድንበሮችን በማጥበብ የወደብ አጠቃቀምን ማቃለል ይቻላል።

ለኢትዮጵያ የታሪክ አደራና የወደፊት ግዴታዋን ለማሳካት በሚደረገው ጉዞ ውስጥ የባሕር በር ማግኘት የሕልውና እና የልማት ጥያቄ ነው።

ይህ ጥያቄ በሰላማዊ ድርድር፣ በዲፕሎማሲያዊ ጥረት፣ በሕጋዊ መንገድና በጋራ እድገት መርህ ላይ ተመስርቶ የሚመለስ ሲሆን፣ በቀጣናው ያሉ ሀገራትም የኢትዮጵያን የባሕር በር ፍላጎት እንደ ስጋት ሳይሆን ለጋራ ልማትና ሰላም እንደታደለ ትልቅ ዕድል በመቁጠር በውይይት ላይ የተመሠረተ ዘላቂ መፍትሔ ማምጣት ይጠበቅባቸዋል።

እስከዚያው ግን ኢትዮጵያውያን የጠላቶቻቸውን ሴራ በማንቃት፣ በብሔራዊ ዓላማችን ዙሪያ በመሰለፍ የሁለተኛው ትውልድ አርበኝነት ግዴታችንን እንወጣለን።

#ትልቅ_ሀገር #ትልቅ_ሕዝብ #ታላቅ_ርዕይ

በአድማሱ አራጋው

 

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: