Search

"የጤና ባለሙያዎቻችንን ማሰልጠን ብቻ ሳይሆን በሀገራቸው እንዲቆዩ ማድረግ ይገባል" - ፕሬዝዳንት ኤቫሪስት ንዳይሺሚዬ

ሰኞ ኅዳር 14, 2019 17

5ኛው ዓለም አቀፍ የአፍሪካ የሕዝብ ጤና ጉባኤ (CPHIA 2026) በአዲስ አበባ አዲስ ዓለም አቀፍ ኮንቬንሽን ማዕከል በዛሬው ዕለት መካሄድ ጀምሯል፡፡ 

የብሩንዲ ፕሬዝዳንትና የወቅቱ የአፍሪካ ሕብረት ሊቀ-መንበር ኤቫሪስት ንዳይሺሚዬ በዚሁ ወቅት፤ የጤና ባለሙያዎቻችንን ማሰልጠን ብቻ ሳይሆን በሀገራቸው እንዲቆዩ ማድረግ ይገባል ብለዋል፡፡

አፍሪካ የጤና ሉዓላዊነቷን ለማረጋገጥ በመድኃኒትና ክትባት ምርት ከውጭ ጥገኝነት መላቀቅ እንዳለባትም አስገንዝበዋል፡፡

በዚህ ረገድ ኮቪድ-19፣ ኤምፖክስ፣ ኮሌራና ኢቦላን የመሳሰሉ ወረርሽኞች አፍሪካ በውጭ ሀገራት በሚመረቱ መድኃኒቶችና ክትባቶች ላይ ያላትን ጥገኝነትና ተጋላጭነት በግልጽ ያሳዩ መሆናቸውን ጠቅሰዋል።

ይህንን ስብራት ለመጠገንም አህጉሪቱ የአፍሪካ አህጉራዊ ነፃ ንግድ ቀጣናን በመጠቀም የጤና ምርቶች የጋራ ገበያ መፍጠር፣ የሀገር ውስጥ የመድኃኒትና ክትባት ምርትን ማስፋፋት እንዲሁም የወረርሽኝ ዝግጁነትና ምላሽ አቅሟን ማጠናከር እንደሚገባት አመልክተዋል።

የጤና ሥርዓቱን በራስ አቅም ለመገንባት የፋይናንስ ቁርጠኝነት ወሳኝ መሆኑን ያነሱት ሊቀ-መንበሩ፣ ከ20 ዓመታት በፊት በአቡጃ በተደረሰው ስምምነት መሠረት የአፍሪካ ሀገራት ከብሔራዊ በጀታቸው ቢያንስ 15 በመቶውን ለጤናው ዘርፍ ለመመደብ የገቡትን ቃል በተግባር እንዲተረጉሙ አሳስበዋል።

ከዚህ ጎን ለጎን የጤና ባለሙያዎችን በብቃት ማሰልጠንና በሀገራቸው እንዲቆዩ ማድረግ እንዲሁም የምርምርና የመረጃ አያያዝ አቅምን ማሳደግ የማይታለፉ ተግባራት መሆናቸውን ገልጸዋል።

 

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: