ሀገራዊ የሥርዓት ግንባታ በአንድ ጀምበር ተገንብቶ የሚያልቅ ሳይሆን ጥበብን፣ ስክነትን፣ ትዕግሥትን እና ትጋትን በተመጣጠነ መልኩ የሚጠይቅ የረጅም ሂደት ጉዞ መሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) አስገነዘቡ።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ባስተላለፉት መልዕክት፣ የ2010 ዓ.ም ሀገራዊ ለውጥ እንዲመጣ ዋነኛ ገፊ ምክንያት የነበረው "እንዴት ወደ ኋላ እንቀራለን?" የሚል ጥልቅ ሀገራዊ ቁጭት እንደነበር አስታውሰዋል።
ይሁን እንጂ ቁጭት የጉዞ መነሻ እንጂ መዳረሻም ሆነ ማድረሻ ሊሆን እንደማይችል ገልጸው፤ የቁጭት ማድረሻው ጠንካራ ሥርዓት፣ የመጨረሻ መዳረሻው ደግሞ ሥልጣኔ መሆኑን አብራርተዋል።
ይህን የሕዝብ ቁጭት ወደ ጠንካራ ሥርዓት አዋላጅነት ለመቀየር ሰክኖ ማሰብ፣ ማሰላሰል፣ መሞከር፣ የተሻለውን መምረጥ እና ዘወትር ማሻሻል ግድ እንደሚልም አጽንኦት ሰጥተውበታል።
በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ ሥርዓት የመገንባት ሙከራ ሲደረግ የቁጭት እጥረት አጋጥሞ እንደማያውቅ የጠቆሙት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ፤ በተቃራኒው ስክነት ማጣት እና ለአዳዲስ ሐሳቦች ዝግ መሆን ጠንካራ ሥርዓት መሠረት እንዳይይዝ ማድረጉን አስረድተዋል።
በተለይም ሀገራዊ ነባራዊ ሁኔታን በሚገባ በመገንዘብ ለኢትዮጵያ አዋጭ የሆነውን መንገድ መርጦ ከመተግበር ይልቅ፣ የኢትዮጵያን ችግር በውጭ ሀገራት ዕይታ ለመፍታት መሞከር በሂደቱ ከፍተኛ ዋጋ ማስከፈሉን አብራርተዋል።
"ምንጩን የሚረሳ ወንዝ እንደሚደርቀው ሁሉ፣ ከሥሩ የተነጠለ ሕዝብ መጨረሻው አያምርም" ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ መሠረቱን፣ ባህሉን፣ ልማዱን እና ሀገራዊ እሳቤውን በመጣል የሚጀመር የሥልጣኔ ጉዞ ሩቅ ሊጓዝ እንደማይችል ገልጸዋል።
ባለፉት ስምንት ዓመታት ኢትዮጵያን ከዚህ አዙሪት ለማውጣት በርካታ ጥረቶች ተደርገው ውጤት መገኘቱን ጠቅሰው፤ በዚህም የኢትዮጵያዊነት መሠረት የሆነውን የመደመር እሳቤ ወደ ሥራ ማስገባት መቻሉን ተናግረዋል።
#ትልቅ_ሀገር! #ትልቅ_ሕዝብ! #ታላቅ_ርዕይ!
በለሚ ታደሰ
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: