Search

ወደ ነገ መሻገር የሚያስችል ታሪካዊ አተያይ በተግባር እየተገነባ ነው፡- ጠቅላይ ሚነስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)

ማክሰኞ መስከረም 26, 2019 110
ከትናንት መልካሙን በመውሰድና ዛሬ ላይ አስፈላጊውን እሴት በመጨመር ወደ ነገ መሻገር የሚያስችል ታሪካዊ አተያይ በተግባር እየተገነባ መሆኑን ጠቅላይ ሚነስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) አስታውቀዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለአዲሱ የሕዝብ ተወካዮች ምክክር ቤት በትናንትናው ዕለት ባደረጉት ንግግር ኢትዮጵያ መፍትሄዋን ከራሷ ማህጸን ማውጣት እንደጀመረች አብስረዋል።
የውጭ ሀገራትን ርዕዮተ ዓለም ገልብጦ በኢትዮጵያ መሬት ላይ ለመትከል የተደረጉ የዘመናት ሙከራዎች፣ ከመልካም ሰብል ይልቅ አረም እያበቀሉ ሀገራችንን ለችግር መዳረጋቸውን አመላክተዋል።
የአውሮፓና የእስያ ስልጣኔዎች የራሳቸውን ባህል መሠረት አድርገው እንደተገነቡት ሁሉ፣ ኢትዮጵያም በራሷ እሴት ላይ የታነጸ 'የመደመር' እሳቤ መከተሏን አብራርተዋል።
ይህ ሀገር በቀል እሳቤ፣ የሕዝቦችን ብዝኃነት ከአንድነት፣ አካባቢያዊነትን ከሀገር እንዲሁም የግል ፍላጎትን ከቡድን ጋር አስተሳስሮ የሚያስኬድ የስልጣኔ ማሰቢያ ቋንቋ መሆኑን አስረድተዋል።
ከባሕር ማዶ የሚመጡ ዕሳቤዎችን አጠቃቀም በተመለከተም ጠቅላይ ሚኒስትሩ "ለሌሎች ዕሳቤ ኢትዮጵያን ከመቀየር ይልቅ ለኢትዮጵያ ሲባል የሌሎችን ዕሳቤ አቃንቶ መቀበል ተገቢ አካሄድ ነው" በማለት ጠንካራ ፖለቲካዊ አቋማቸውን አንጸባርቀዋል።
በዚህም መሠረት ትናንትን ሙሉ በሙሉ እንደ እርኩስ ወይም እንደ ቅዱስ ከሚቆጥረው የጽንፍ ፖለቲካ በመውጣት፣ ከትናንት መልካሙን በመውሰድና ዛሬ ላይ አስፈላጊውን እሴት በመጨመር ወደ ነገ መሻገር የሚያስችል ታሪካዊ አተያይ በተግባር እየተገነባ መሆኑን ተናግረዋል።
 
በበረከት ሽመልስ
 
 

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: