Search

የኢትዮጵያን የአቪዬሽን መሪነት ወደ ዓለም አቀፍ ውሳኔ ሰጪነት ያሳደገው ታሪካዊ ምርጫ

ማክሰኞ ኅዳር 15, 2019 67

ኢትዮጵያ ኅዳር 11 ቀን 2019 ዓ.ም በካናዳ ሞንትሪያል በተካሄደው የዓለም አቀፍ ሲቪል አቪዬሽን ድርጅት (ICAO) ጠቅላላ ጉባኤ ልዩ ስብሰባ ላይ የካውንስሉ አባል ሆና ተመርጣለች።

ከ193 አባል መንግሥታት መካከል ከቱርኪዬ ጋር እኩል 133 ድምፅ በማግኘት ከፍተኛውን ውጤት የተጋራች ሲሆን፣ ኦማን 125 እንዲሁም ኢንዶኔዥያ 110 ድምፅ አግኝተዋል።

ምርጫው የተካሄደው የቺካጎ ስምምነት አንቀጽ 50(a) ማሻሻያ ሰኔ 5 ቀን 2018 ዓ.ም ሥራ ላይ በመዋሉ የካውንስሉ መቀመጫዎች ከ36 ወደ 40 በማደጋቸው ነው።

ሁሉም የዓለም ክፍሎች እንዲወከሉ በሚያደርገው ክፍል ሦስት ሥር በተጨመሩት አራት አዳዲስ መቀመጫዎች፣ ኢትዮጵያ ብቸኛዋ የአፍሪካ እጩ ሆና ቀርባ አሸንፋለች።

በ1937 ዓ.ም የድርጅቱ መሥራች አባል የሆነችው ኢትዮጵያ፣ ከ1994 እስከ 1999 ዓ.ም ለሁለት ዙር እንዲሁም በ2015 ዓ.ም በካውንስሉ አገልግላለች። የአሁኑ የሥራ ዘመኗም እስከ 2021 ዓ.ም 44ኛው መደበኛ ጉባኤ ድረስ ይቀጥላል።

የ133ቱ ድምፅ ስኬት የተቀናጀ ዲፕሎማሲ ፍሬ ነው። የአፍሪካ ኅብረት ኢትዮጵያን የአህጉሪቱ ብቸኛ እጩ አድርጎ ማቅረቡ እና የአፍሪካ ሲቪል አቪዬሽን ኮሚሽን (AFCAC) ያደረገው ድጋፍ የድምፅ መከፋፈልን አስቀርቷል። በዚህም በ40 አባላት በተዋቀረው ካውንስል ውስጥ የአፍሪካን መቀመጫ ወደ 9 በማሳደግ የአህጉሪቱን ድርሻ ወደ 22.5 በመቶ ከፍ አድርጋለች።

በተጨማሪም ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በተሳተፉበት እና መስከረም 2 እና 3 ቀን 2019 ዓ.ም በኒው ዴሊ በተካሄደው 18ኛው የብሪክስ ጉባኤ የተላለፈው መግለጫ የኢትዮጵያን እጩነት በግልጽ ደግፏል።

የአፍሪካ እና የብሪክስ አባላት ጠቅላላ ቁጥር ከ133 እጅግ ያነሰ መሆኑ፣ ድሉ ከእነዚህ ቡድኖች ውጭ ካሉ በርካታ መንግሥታት ጋር የተሠራ ሰፊ የሁለትዮሽ ዲፕሎማሲ ውጤት መሆኑን ያረጋግጣል።

ኢትዮጵያ እጩ ሆና የቀረበችው በመሥራች አባልነቷ ብቻ ሳይሆን በተጨባጭ የዘርፉ ዕድገት ላይ ተመሥርታ ነው።

ICAO ከጥቅምት 4 እስከ 17 ቀን 2019 ዓ.ም በኢትዮጵያ ሲቪል አቪዬሽን ባለሥልጣን ላይ ባካሄደው የደኅንነት ቁጥጥር ኦዲት (USOAP-CMA) 85.76 በመቶ አጠቃላይ ውጤታማ አፈጻጸም አስመዝግባለች። ይህ ውጤት በ2007 ዓ.ም ከተመዘገበው 62.92 በመቶ ጋር ሲነጻጸር የ22.84 ነጥብ ዕድገት አሳይቷል።

በንግዱ መስክ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ በ2018 በጀት ዓመት ገቢውን በ20 በመቶ አሳድጎ 9.1 ቢሊዮን ዶላር አድርሷል። በዓመቱ 20.7 ሚሊዮን መንገደኞችን እና 897 ሺህ ቶን ጭነትን ያጓጓዘ ሲሆን፣ ዓለም አቀፍ መዳረሻዎቹም 150 ደርሰዋል።

ምርጫው በተካሄደበት ሳምንት በሲንጋፖር በተደረገው መድረክ የ2027 ባለ አምስት ኮከብ ዓለም አቀፍ አየር መንገድ እና የአፍሪካ ምርጥ አጠቃላይ አየር መንገድ ሽልማቶችን ተቀዳጅቷል። ከናይጄሪያው ኤር ፒስ ጋር የፈረመው የኢንተርላይን ስምምነት እና በኤር ኮንጎ ያለው የ49 በመቶ ድርሻም አህጉራዊ ተጽዕኖውን ያጎላል።

በመሠረተ ልማት ረገድ ጥር 2 ቀን 2018 ዓ.ም ግንባታው የተጀመረው የ12.5 ቢሊዮን ዶላሩ የቢሾፍቱ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ የመጀመሪያ ምዕራፍ በ2022 እና በ2023 ዓ.ም መካከል ተጠናቅቆ ለ60 ሚሊዮን መንገደኞች አገልግሎት ይሰጣል።

ሁለተኛው ምዕራፍ ሲጠናቀቅ 110 ሚሊዮን መንገደኞችን የማስተናገድ አቅም ይኖረዋል። ይህም ከኢትዮጵያ አቪዬሽን ዩኒቨርሲቲ የሰው ኃይል ልማት እና ከአውሮፕላን ጥገና ማዕከል አቅም ጋር ተዳምሮ ዘላቂ መሠረት እየጣለ ነው።

የICAO ካውንስል የድርጅቱ ቋሚ የአስተዳደር አካል ሲሆን፣ ኢትዮጵያ በዚህ ጠረጴዛ ዙሪያ መቀመጧ በርካታ ስትራቴጂያዊ ጥቅሞች ያስገኝላታል፡፡

በበረራ ደኅንነት፣ በአቪዬሽን ጸጥታ፣ በአየር አሰሳ እና በአካባቢ ጥበቃ ዙሪያ የሚተገበሩ ዓለም አቀፍ ደረጃዎች እና የሚመከሩ አሠራሮች (SARPs) ገና ሲረቀቁ ብሔራዊ ጥቅሟን እንድታስከብር ያስችላታል።

የአየር አሰሳ ኮሚሽን (ANC) አባላት ከ19 ወደ 21 ሲያድጉ ሹመቱን የሚሰጠው ካውንስሉ በመሆኑ፣ በዓለም አቀፉ የአቪዬሽን ቴክኒክ አመራር ምደባ ላይ ቀጥተኛ ድምፅ እና ተጽዕኖ ይኖራታል።

ዓለም አቀፍ የአውሮፕላን ማረፊያ ፋይናንስ መመሪያዎች ሲቀረጹ እንደ ቢሾፍቱ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ላሉ ግዙፍ ፕሮጀክቶች ምቹ የፋይናንስ ሥርዓት እንዲፈጠር ቀጥተኛ ሚና ትጫወታለች።

በካርቦን ማካካሻ (CORSIA) እና በዘላቂ የአቪዬሽን ነዳጅ (SAF) ደንቦች ዙሪያ የአፍሪካን የምርት እና የፋይናንስ አቅም ያገናዘበ ፍትሐዊ የአረንጓዴ ሽግግር ደንብ እንዲቀረጽ ለመሟገት ሰፊ መድረክ ይፈጥርላታል።

ይህ ታሪካዊ ስኬት ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ የአየር ትራንስፖርት ፖሊሲ ቀረጻ ውስጥ ያላትን መሪነት በማጽናት፣ ለራሷም ሆነ ለመላው አፍሪካ አቪዬሽን ዕድገት አዲስ ምዕራፍ የሚከፍት ነው።

በለሚ ታደሰ

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: