ዲጂታል ቴክኖሎጂ እና ሰው ሠራሽ አስተውሎት (AI) የጤና አገልግሎትን ተደራሽ፣ ቀልጣፋ አና ጥራት ያለው በማድረግ ወሳኝ ሚና እየተወጡ ነው።
ኢትዮጵያም ይህን የዘመኑን ዕድል በመጠቀም ከወረቀት ወደ ዲጂታል ሥርዓት፣ ከባህላዊ አሠራር ወደ ዘመናዊ የሕክምና መፍትሔ የሚያሸጋግሯትን ሥራዎች በማከናወን ላይ ትገኛለች።
ጥረቱ በአራት መሠረቶች ላይ የቆመ ነው። እነሱም የዲጂታል ጤና መሠረተ ልማትን ማስፋፋት፣ የጤና መረጃ አያያዝን ማዘመን፣ ሰው ሠራሽ አስተውሎትን በበሽታ ምርመራ እና በምርምር ማዋል፣ እንዲሁም የራስን የቴክኖሎጂ አቅም መገንባት ናቸው።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የአፍሪካ ኅብረት የሰው ሠራሽ አስተውሎት እና የዲጂታል ጤና መሪ (ሻምፒዮን) ሆነው መሾማቸው፣ ኢትዮጵያ በዘርፉ የምታከናውነውን እና በአህጉሪቱ የምትወስደውን የመሪነት ሚና ያጎላ ነው።
ከዲጂታል ጤና ሽግግሩ ስኬቶች አንዱ የጤና መረጃ ሥርዓትን ማዘመን ነው። የዲስትሪክት ጤና መረጃ ሶፍትዌር (DHIS2) የጤና ተቋማትን በተቀናጀ የመረጃ ሥርዓት በማገናኘት፣ የበሽታ ሥርጭትን ለመከታተል እና የመድኃኒት አቅርቦትን ከፍላጎት ጋር ለማጣጣም እያገዘ ነው።
የቴሌ-ጤና (telemedicine) አገልግሎት መስፋፋትም ራቅ ባሉ አካባቢዎች የሚኖሩ ማኅበረሰቦችን ከስፔሻሊስት ሐኪሞች ጋር በዲጂታል አማራጮች እንዲገናኙ በማስቻል የርቀት ችግርን እያጠበበ ነው።
የዘመናዊ ሕክምና አቅም አንዱ ማሳያ በግንቦት ወር የተመረቀው የላፍቶ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል ነው። በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የተገነባው ሆስፒታሉ በ5.4 ሄክታር መሬት ላይ በ17 ሕንፃዎች የተዋቀረ ሲሆን፣ 500 አልጋዎች አሉት።
በካንሰር እና በልብ ሕክምና ላይ ያተኮረው ተቋሙ በሰው ሠራሽ አስተውሎት የታገዘ PET-SCAN፣ ባለ3 ቴስላ MRI፣ ባለ640 ስላይስ CT scan እና አውቶሜትድ የላቦራቶሪ ሥርዓትን ጨምሮ ዘመናዊ የምርመራ መሣሪያዎች ተገጥመውለታል። ይህም ዜጎች ለሕክምና ወደ ውጭ የሚያደርጉትን ጉዞ በመቀነስ የውጭ ምንዛሬን ለመቆጠብ ያግዛል።
በትላልቅ ሆስፒታሎች እየተዘረጋ ያለው የኤሌክትሮኒክ የሕክምና መዝገብ ሥርዓትም የታካሚዎችን የሕክምና ታሪክ በተቀናጀ መልኩ ለማየት እና ከአንዱ የሕክምና ክፍል ወደ ሌላው መረጃ በፍጥነት ለማስተላለፍ ያስችላል። የወረቀት አጠቃቀምን በመቀነስ የመረጃ ጥራትን፣ የውሳኔ አሰጣጥን እና የአገልግሎት ቅልጥፍናን ያሻሽላል።
ሰው ሠራሽ አስተውሎትን በጤናው ዘርፍ ለማልማት የተጀመሩ ሥራዎችም አዲስ የመፍትሔ አቅም እየፈጠሩ ነው። የኢትዮጵያ ሰው ሠራሽ አስተውሎት ኢንስቲትዩት የጡት ካንሰርን እና የስኳር በሽታን ለመለየት የሚያግዙ መሣሪያዎችን አበልጽጎ የፓተንት መብት አግኝቷል።
የሳንባ ነቀርሳ ምርመራን ለማገዝም ሥራዎች እየተከናወኑ ነው። እነዚህ ቴክኖሎጂዎች ምርመራን በማፋጠን፣ የስፔሻሊስት ባለሙያዎችን እጥረት በመቅረፍ እና ሕክምናን በጊዜ ለመጀመር በማስቻል ትልቅ አስተዋጽኦ ያበረክታሉ።
በአዲስ አበባ እየተካሄደ ያለው አምስተኛው የአፍሪካ የሕዝብ ጤና ጉባኤ (CPHIA 2026) በዚህ የለውጥ ጉዞ ውስጥ ልዩ ፋይዳ አለው። በአፍሪካ ሲዲሲ (Africa CDC) እና በኢትዮጵያ መንግሥት በጋራ የተዘጋጀው ጉባኤ "የአፍሪካ የጤና ደኅንነት እና ሉዓላዊነት" በሚል መሪ ሐሳብ፣ የአፍሪካ ሀገሮች ከውጭ ድጋፍና ከመድኃኒት፣ ከክትባት እና ከሕክምና መሣሪያዎች ጥገኝነት ተላቅቀው በራሳቸው ሀብት፣ ዕውቀት እና የማምረት አቅም የሕዝቦቻቸውን ጤና የሚጠብቁበት ዘላቂ ሥርዓት እንዲገነቡ ለማበረታታት ያለመ ነው።
በዚህም በባለፈው ዓመት የደርባን ጉባኤ የተያዙትን የጤና ምርቶች ማምረት፣ የጤና ፋይናንስ፣ የመጀመሪያ ደረጃ ጤና አገልግሎት፣ የወረርሽኝ ዝግጁነት እና የመረጃ ባለቤትነት ቅድሚያ ጉዳዮች ወደ ተግባር የመለወጥ ሚና ይጠበቅበታል። ይህም ኢትዮጵያ በቀጣይ በጤናው ዘርፍ የምትሠራቸውን ሥራዎች የሚያጠናክር መድረክ ነው።
ኢትዮጵያ በዲጂታል ጤና እና በሰው ሠራሽ አስተውሎት የምታከናውነው ሥራ የጤና አገልግሎትን ከማዘመን ባለፈ፣ የቴክኖሎጂ ሉዓላዊነትን እና የራስን አቅም የመገንባት ቁርጠኝነቷን የሚያሳይ ነው።
የጉዞው ዋነኛ ግብም የቴክኖሎጂ ስኬትን ወደ ተጨባጭ የሕዝብ ጥቅም በመለወጥ ለሁሉም ዜጋ ፍትሐዊ፣ ተደራሽ እና ጥራት ያለው የጤና አገልግሎት ማረጋገጥ ነው።
በብሌን ደምበሎ
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: