የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት በ2019 በጀት ዓመት ጥቅምት ወር ብቻ 66 ሺህ 473 አዳዲስ ደንበኞችን ከኤሌክትሪክ መረብ ጋር በማገናኘት የኤሌክትሪክ ተጠቃሚ ማድረግ ችሏል።
በዚህም በወሩ 88 ሺህ 253 አዳዲስ ደንበኞችን የኤሌክትሪክ ተጠቃሚ ለማድረግ አቅዶ 75.3 በመቶ ማሳካት መቻሉን አስታውቋል።
የወሩ አፈጻጸም ከ2018 በጀት ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር 20 ሺህ 23 ተጨማሪ ደንበኞችን የኤሌክትሪክ ተጠቃሚ ማድረግ መቻሉን እንደሚያሳይ አመልክቷል።
በወሩ አዲስ ከኤሌክትሪክ መረብ ከተገናኙት ደንበኞች መካከል 62 ሺህ 574 የቅድመ ክፍያ ቆጣሪዎች፣ ቀሪዎቹ 3 ሺህ 899 ደግሞ የድኅረ ክፍያ ቆጣሪዎች ተገጥመውላቸዋል።
ከአዲስ ደንበኞች ውስጥ 92.3 በመቶ በኦፖሬሽን የተስተናገዱ ሲሆን፣ ቀሪዎቹ 7.7 በመቶ ደንበኞች ደግሞ በፕሮጀክት አማካኝነት አገልግሎቱን ማግኘታቸው ተገልጿል።
በዚህም መሠረት እስከ 2019 በጀት ዓመት ጥቅምት ወር መጨረሻ ድረስ የተቋሙ አጠቃላይ ደንበኞች ብዛት 6 ሚሊዮን 90 ሺህ 965 መድረሱን አገልግሎቱ ለኢቢሲ ዶትስትሪም በላከው መረጃ ጠቁሟል።
የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት እያከናወነ ያለው የአዳዲስ ደንበኞች የኃይል ማገናኘት ሥራ የዜጎችን የኑሮ ደረጃ ከማሻሻል ባሻገር የንግድና የኢንዱስትሪ እንቅስቃሴን፣ የማኅበራዊ አገልግሎቶችንና አጠቃላይ የኢኮኖሚ እድገትን በመደገፍ ለሀገራዊ ልማት ወሳኝ አስተዋጽኦ እንደሚያበረክትም አብራርቷል።
በመሆኑም ተቋሙ የኤሌክትሪክ ተደራሽነትን ለማስፋትና የኃይል አገልግሎትን ለብዙ ዜጎች ለማዳረስ የጀመረውን ጥረት አጠናክሮ እንደሚቀጥል ገልጿል።
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: