Search

ሚኒስትሮች ከሚመሩት መሥሪያ ቤት እና ከዘመኑ ጋር አብረው እንዲራመዱ ለማድረግ ሰፊ ጥረት ተደርጓል፡- ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)

ሓሙስ መስከረም 28, 2019 129

ሚኒስትሮች ከሚመሩት መሥሪያ ቤት እና ከዘመኑ ጋር አብረው እንዲራመዱ ለማድረግ ሰፊ ጥረት መደረጉን ጠቅላይ ሚኒስትር  ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) አስታውቀዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ የካቢኔ አባላትን ለሕዝብ ተወካዮች ምክርት ቤት ባቀረቡበት ወቅት፣ ዛሬ የተሾሙት የካቢኔ አባላት ከፍተኛ አደራ የተጣለባቸው፣ ሹመት መቀበል ትልቅ ኃላፊነትና ሸክም መሆኑን እንዲገነዘቡ አሳስበዋል።

ሹመት የምንዝናናበት ሳይሆን ቀንና ሌሊት የምንሠራበት እና የምንፈጋበት መሆን አለበት ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር  ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)፣  ኢትዮጵያን ለማጽናት፣ ለማበልጸግና ወደ ታላቅ ሥልጣኔ የማሸጋገር ጉዟችንን ለማፋጠን ከፍተኛ ጥረት የሚደረግበት መሆኑንም አስረድተዋል።

ሹመት ብዙ ምቾት፣ እንቅልፍ እና ድሎት ያለው ጉዳይ ሳይሆን፣ ሰፊ ኃላፊነትና ድካም ያለበት መሆኑን እያንዳንዱ የካቢኔ አባል ከወዲሁ እንዲገነዘብ፤ የምክር ቤት አባላትም ይህንን ታሳቢ አድርገን ለመሥራት ያደረግነውን ጥረት ከግምት እንዲያስገባ አሳስበዋል።

ሚኒስትሮች ከሚመሩት መሥሪያ ቤት እና ከዘመኑ ጋር አብረው እንዲራመዱ ለማድረግ ሰፊ ጥረት መደረጉን ገልጸው፣ የሚቀጥሉት አሥር ዓመታት ብዙ ሩጫና ጥረት የሚጠይቁ መሆናቸውን አስገንዝበዋል።

የኢትዮጵያ እድገት፣ ለውጥና መሻሻል እያንዳንዱን ዜጋ የማይነካ ከሆነ ዋጋ የለውም ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ፣  ዜጎችን በቀጥታ የሚነካ እድገት ለማምጣት፣ በሂደትና በውጤቱ ብቻ የሚረኩ ሳይሆኑ፣ የሚመጣውን ተጽዕኖ መለካት የሚችሉ ግለሰቦች እንዲሆኑ ጥረት ተደርጓል ብለዋል።

በመሐመድ ፊጣሞ

 

 

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: