የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በዛሬው ዕለት ባካሄደው 1ኛ መደበኛ ስብሰባው በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የቀረቡለትን የአዲሱ የመደመር መንግሥት ካቢኔ አባላት ሹመት አጽድቋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ዕጩ የካቢኔ አባላቱን ለምክር ቤቱ ባቀረቡበት ወቅት እንደገለጹት፣ የኢትዮጵያን መሻት ለማሳካትና የዜጎችን ጥቅም ለማስፈጸም በሚደረገው ጉዞ ብዝሃነትን ታሳቢ ያላደረገ አካሄድ ኅብረ-ብሔራዊት ኢትዮጵያን በአግባቡ ማንፀባረቅ አይችልም።
በመሆኑም በአዲሱ የካቢኔ ሹመት መመዘኛ መስፈርት ከዕጩዎቹ የትምህርት ዝግጅትና የመፈጸም አቅም በተጨማሪ በተቻለ መጠን የብሔር፣ የፆታ እና የእምነት ስብጥርን ለመጠበቅ ጥረት መደረጉን አስረድተዋል።
በአዲሱ የካቢኔ ውቅር ለዘመናት ትኩረት አግኝተው የማያውቁና ላለፉት ከ30 ዓመታት በላይ በካቢኔ ደረጃ ታሳቢ ያልተደረጉ ክልሎች ተወካዮች ወደ ከፍተኛ አመራርነት እንዲመጡ መደረጉን ጠቅላይ ሚኒስትሩ ገልጸዋል።
በተጨማሪም ሀገር የጋራ በመሆኗ የፖለቲካ ምህዳሩን ለማስፋትና የነቃ ተሳትፎን ለማጎልበት ሲባል የተፎካካሪ ፖለቲካ ፓርቲዎች አመራሮች በካቢኔው ውስጥ እንዲካተቱ ተደርጓል።
በመደመር መንግሥት ሥርዓት ዜጎች በተሰማሩበት ሙያና መስክ የካበተ ዕውቀት ያላቸው በመሆናቸው ሀገራቸውን እንዲያገለግሉ ዕድል በመስጠት ኅብረ-ብሔራዊ አንድነትን የማጠናከር ሥራ ተሰርቷል።
የተሾሙት የካቢኔ አባላት ህዝብና ሀገር የጣሉባቸውን ከፍተኛ አደራና ኃላፊነት በአግባቡ የማይወጡ ከሆነ እርምጃ እንደሚወሰድባቸው ጠቅላይ ሚኒስትሩ አረጋግጠዋል።
በሜሮን ንብረት
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: