የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች የወደፊት ዕጣ ፈንታ ሲነሣ እንደ ኖርዌይ፣ ቻይና እና አሜሪካ ያሉ የበለጸጉ ሀገራት በቀዳሚነት ይጠቀሳሉ።
ይሁን እንጂ በዓለም አቀፍ ደረጃ በከፍተኛ ፍጥነት ወደ ኤሌክትሪክ ተሽከርካሪነት እየተሸጋገረች ያለችው ሀገር በኢኮኖሚ ያልበለጸገችው እና በመኪና ምርት የማትታወቀው ኢትዮጵያ መሆኗን የዓለማችን ግዙፉ የሚዲያ ተቋም ብሉምበርግ (Bloomberg) በልዩ ዘገባው ይፋ አድርጓል።
እ.አ.አ. በ2024 ኢትዮጵያ በነዳጅ የሚሠሩ አዳዲስ የቤት መኪኖች ወደ ሀገር ውስጥ እንዳይገቡ ሙሉ በሙሉ በማገድ በዓለም የመጀመሪያዋ ሀገር ሆናለች።
እንደ እንግሊዝ፣ ካናዳ እና የአውሮፓ ኅብረት አባል ሀገራት ተመሳሳይ እርምጃ ለመውሰድ የዐሥርተ ዓመታት ዕቅድ አውጥተው ዛሬም ድረስ እያመነቱ በሚገኙበት ወቅት፣ ኢትዮጵያ ውሳኔውን በአንድ ጀምበር ተግባራዊ አድርጋዋለች።
የብሉምበርግ ዘገባ እንደሚያመለክተው፣ የመደመር መንግሥት ይህንን እርምጃ የወሰደው ከአየር ንብረት ጥበቃ ባለፈ በከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ እጥረት ተገድዶ ነው። ኢትዮጵያ በየዓመቱ እስከ 5 ቢሊዮን የአሜሪካ ዶላር ለነዳጅ ግዢ የምታወጣ ሲሆን፣ ለዓመታት ስታደርገው የነበረው የነዳጅ ድጎማ ኢኮኖሚውን ክፉኛ ጎድቶታል።
የነዳጅ መኪኖች እንዳይገቡ የተወሰደው እገዳ በአዲስ አበባ ጎዳናዎች ላይ ፈጣን ለውጥ አምጥቷል። በ2022 በመላ ኢትዮጵያ 7 ሺህ ብቻ የነበረው የኤሌክትሪክ መኪኖች ቁጥር፣ በፈረንጆቹ 2025 ደግሞ ከ100 ሺህ በላይ መሻገሩን የመንግሥት መረጃዎች ያሳያሉ።
በአሁኑ ወቅት በአዲስ አበባ ከሚመዘገቡ አዳዲስ መኪኖች ውስጥ ከ60 በመቶ በላይ የሚሆኑት የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች ናቸው። ይህም በኢትዮጵያ አጠቃላይ የተሽከርካሪዎች ድርሻ ውስጥ የኤሌክትሪክ መኪኖችን ወደ 6 በመቶ ያሳደገው ሲሆን፣ ከዓለም አቀፉ አማካይ (4 በመቶ) የበለጠ ነው።
የሕዳሴ ግድብ በረከት እና የመሠረተ ልማት ፈተናዎች
ኢትዮጵያ ለነዳጅ የሚሆን ዶላር ቢያጥራትም፣ በዓለም ላይ ካሉት እጅግ ርካሽ የኤሌክትሪክ ኃይል አቅራቢዎች አንዷ ናት። በአሜሪካ አንድ ኪሎዋት ሰዓት ኤሌክትሪክ በአማካይ 18 ሳንቲም፣ በእንግሊዝ ደግሞ 40 ሳንቲም ሲሸጥ፣ በኢትዮጵያ ግን ወደ 10 የአሜሪካ ሳንቲም ገደማ ነው።
የዚህ ዋነኛ ምንጭ ደግሞ ከ5 ሺህ ሜጋ ዋት በላይ የማመንጨት አቅም ያለው ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ነው። በአሁኑ ሰዓት በአዲስ አበባ፣ አዳማ እና ሐዋሳን ጨምሮ ወደ 200 የሚጠጉ የኤሌክትሪ መኪና ቻርጅ ማድረጊያ ጣቢያዎች ብቻ ይገኛሉ።
በአዲስ አበባ የመኪና መሸጫዎች የሚታዩት አብዛኞቹ የኤሌክትሪክ መኪኖች ከቻይና የሚገቡ ናቸው። መንግሥት መኪኖቹ በሀገር ውስጥ እንዲገጣጠሙ ለማበረታታት ልዩ የታሪፍ አሠራር ዘርግቷል፦
ሙሉ በሙሉ የተገጣጠመ የኤሌክትሪክ መኪና ሲገባ፦ 15% ቀረጥ
በከፊል የተበታተነ (SKD) ሲገባ፦ 5% ቀረጥ
ሙሉ በሙሉ የተበታተነ (CKD) ሲገባ፦ 0% ቀረጥ (ከቀረጥ ነፃ)
ይህንን ዕድል በመጠቀም እንደ በላይነህ ክንድዬ ግሩፕ (BKG) ያሉ የሀገር ውስጥ ኩባንያዎች ከቻይናው ‘ናንጂንግ ጎልደን ድራጎን’ ጋር በመተባበር የኤሌክትሪክ ሚኒባሶችን በሀገር ውስጥ በመገጣጠም ለገበያ እያቀረቡ ይገኛሉ።
ኢትዮጵያ እስከ 2033 ዓ.ም (እ.አ.አ) የኤሌክትሪክ መኪኖችን ቁጥር 500 ሺህ ለማድረስ አቅዳለች።
በመካከለኛው ምሥራቅ ግጭት ምክንያት የዓለም የነዳጅ ዋጋ እስከ 50 በመቶ ማሻቀቡ የኢትዮጵያን ውሳኔ ትክክለኛነት እያረጋገጠ መጥቷል። እ.አ.አ በ2027 የተባበሩት መንግሥታት የአየር ንብረት ጉባኤን (COP) በአዲስ አበባ የምታስተናግደው ኢትዮጵያ፣ በማደግ ላይ ያሉ ሀገራት እንዴት ወደ አረንጓዴ ኢኮኖሚ መሸጋገር እንደሚችሉ ለዓለም ለማሳየት በዝግጅት ላይ ትገኛለች።
በነቢዩ ወንድወሰን
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: