አዲስ አበባ በከተማ ልማት የጀመረችው ጉዞ የአንድን ከተማ ገጽታ ከመቀየር ባለፈ፣ የከተማ ልማት ምን ያህል የዜጎችን ሕይወት መለወጥ፣ የኢኮኖሚ እድገትን ማፋጠን እና ለቀጣይ ትውልድ የተሻለ ከተማ መገንባት እንደሚችል የሚያሳይ ተግባራዊ ምሳሌ ሆኗል።
በተቋማዊ አቅም ግንባታ፣ በተቀናጀ መሠረተ ልማት ዝርጋታ፣ በአገልግሎት አሰጣጥ ማዘመን፣ በቴክኖሎጂ አጠቃቀምና በከተማ አስተዳደር ብቃት ረገድ የተከናወኑ ሥራዎች ከተማዋን ወደ አዲስ የልማት ምዕራፍ አሸጋግረዋል።
የመንገድ፣ የውኃ፣ የፍሳሽ፣ የመብራት፣ የትራንስፖርትና የዲጂታል መሠረተ ልማቶችን በተቀናጀ መልኩ ማስፋፋት የከተማዋን ተደራሽነት፣ የኢኮኖሚ እንቅስቃሴና የአገልግሎት ጥራት እያሳደጉ ነው።
በአካባቢ ጥበቃና በአረንጓዴ ልማት ረገድ የተከናወኑ ሥራዎችም የከተማዋን ውበት ከማሻሻል ባለፈ፣ ለአየር ንብረት ለውጥ መላመድና ተፅዕኖውን መቀነስ ጉልህ አስተዋፅኦ እያደረጉ ነው።
በዚህም አዲስ አበባ በአለምአቀፍ ደረጃ እውቅናዎችን በተከታታይ አመታት በተለያዩ ዘርፎች እንድታገኝ አድርገዋታል።
በተለይም የተበከሉ ወንዞችን በማጽዳት፣ የወንዝ ዳርቻዎችን በማልማትና ወደ መዝናኛ፣ መስተንግዶና የቱሪዝም ማዕከላት በመቀየር ከተማዋ ከተፈጥሮ ጋር ያላትን ግንኙነት እያደሰች ትገኛለች።
ከዚህም በላይ የመዝናኛ ስፍራዎችን፣ የቱሪዝም መዳረሻዎችን፣ የባህልና ታሪካዊ ቅርሶችን በተቀናጀ የመንገድና የእግረኛ መሠረተ ልማት ማገናኘት የከተማዋን የመሠረተ ልማት መስተጋብር (Connectivity) በማሳደግ ለነዋሪዎችና ለጎብኚዎች የተሻለ የእንቅስቃሴና የመዝናኛ አማራጭ ፈጥሯል።
የእነዚህ ልማቶች ዋነኛ ዓላማ ዜጎችን ሁለንተናዊ ተጠቃሚ ማድረግ፣ ለሁሉም እኩል የሆነ የእድል ተደራሽነት መፍጠር፣ የሥራ እድልን ማስፋፋትና አካታች የኢኮኖሚ እድገትን ማረጋገጥ ነው።
ዛሬ አዲስ አበባ እየተጓዘችበት ያለው የልማት ጉዞና ያስመዘገበችው ውጤት ለሌሎች የአፍሪካ ከተሞች የመነቃቃት፣ የመማርና የመለወጥ ተስፋ እየፈጠረ ነው።
ይህም አዲስ አበባ የአፍሪካውያን የጋራ መዲና ብቻ ሳትሆን፣ የዘመናዊ ከተማ ልማት፣ የሥልጣኔ፣ የአካታችነትና የዘላቂ እድገት ማሳያ እየሆነች መምጣቷን ያረጋግጣል።
አዲስ አበባ፤ ለአፍሪካ የለውጥ ተስፋ፣ ለዘላቂ ልማት ተግባራዊ ምሳሌ!
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: