በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ባለፉት ሦስት ዓመታት የጤና ተቋማትና አገልግሎት አሰጣጥ አበረታች ዕድገት ማሳየቱን የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር የትምጌታ አስራት(ዶ/ር)ገለጹ።
የኢትዮጵያን ሁለንተናዊ ብልፅግና እውን ማድረግ የሚቻለው አካላዊና አዕምሯዊ ጤንነቱ የተጠበቀ ብቁና ንቁ ዜጋ ሲገነባ መሆኑንም ተናግረዋል።
በሆሳዕና ከተማ "እምርታዊ ሪፎርም ለሉዓላዊና የማይበገር የጤና ሥርዓት" በሚል መሪ ቃል በይፋ በተከፈተው 28ኛው ዓመታዊ የጤና ጉባኤ ላይ ተኝተው ንግግር ያደረጉት ርዕሰ መስተዳድሩ፤ ከዚሁ መርህ በመነሳት የጤናው ዘርፍ ዘመኑን የዋጀና የኅብረተሰቡን እርካታ የሚያረጋግጥ እንዲሆን በርካታ ዘርፈ-ብዙ ሥራዎች እየተከናወኑ እንደሚገኙ ጠቁመዋል።
አያይዘውም ተለዋዋጭ በሆነው ዓለም አቀፋዊ ሁኔታ ውስጥ በአሠራር፣ በአደረጃጀትና በሰው ኃይል የተጠናከረ እንዲሁም ዘመናዊ የዲጂታል ጤና ሥርዓት መገንባት አስፈላጊ መሆኑን አስገንዝበዋል።
ቀደም ሲል የነበረውን የጤና ፖሊሲ በማዳበር በሽታን ከመከላከል ባለፈ አክሞ በማዳን እንዲሁም ሁሉንም በሽታዎች በመከላከልና በመቆጣጠር ላይ ትኩረት እንዲደረግ ምቹ ሁኔታዎች መፈጠራቸውን አብራርተዋል።
ክልሉ ባለፉት ሦስት ዓመታት ባደረገው አበረታች እንቅስቃሴ የኮምፕሬንሲቭ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታሎች ቁጥር ከ1 ወደ 3፣ የመጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታሎች ከ19 ወደ 25፣ የጤና ጣቢያዎች ከ219 ወደ 244፣ የኮምፕሬንሲቭ ጤና ኬላዎች ከ6 ወደ 25፣ እንዲሁም ሞዴል የማኅበረሰብ መድኃኒት ቤቶች ከ5 ወደ 40 ማደጋቸውን አመልክተዋል።
በተጨማሪም በኅብረተሰቡ ንቁ ተሳትፎ የበርካታ ሆስፒታሎች፣ የጤና ጣቢያዎች፣ የጤና ኬላዎችና የመድኃኒት ቤቶች ግንባታ እንዲሁም የሕክምና ቁሳቁስ የማሟላት ሥራዎች እየተከናወኑ እንደሚገኙ ገልጸዋል።
በሌላ በኩል የእናትና ሕፃናት ሞትን የመቀነስ ግብ አስቀድሞ መሳካቱን የጠቆሙት ርዕሰ መስተዳድሩ፤ የማኅበረሰብ አቀፍ የጤና መድን አባላት ምጣኔ ከ71 በመቶ ወደ 84.2 በመቶ ከፍ ማለቱን ተናግረዋል።
የዜጎችን ጤና የመገንባት ጉዳይ ከጤና ሴክተር ባለፈ የምግብ ሉዓላዊነትን ከማረጋገጥ ጋር የተያያዘ በመሆኑ፤ ባለድርሻ አካላት፣ ሴክተሮች፣ የክልልና የከተማ አስተዳደሮች እንዲሁም አጋር ድርጅቶች ጠንካራ ቅንጅት ፈጥረው በጋራ እንዲሠሩ ጥሪ አቅርበዋል።
በብሌን ደምበሎ
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: