Search

ዓለም የኢትዮጵያን ሕዝብ ቢከተል ምድራችን 3.58 ትሪሊዮን ችግኞች በኖራት ነበረ

ሓሙስ ኅዳር 03, 2019 85

ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ በአየር ንብረት ለውጥ ዙሪያ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጠነከረ በሚመጣ አስደንጋጭ ቀውስ ውስጥ ይገኛል።

በቱርክ አንታሊያ እየተካሄደ በሚገኘው 31ኛው የተባበሩት መንግሥታት የአየር ንብረት ለውጥ ጉባኤ (COP31) ላይ እንደተስተዋለው የዓለም መንግሥታት የልቀት መጠንን ለመግታት የገቡት ቃል እና ያቀረቧቸው የድርጊት መርሐ ግብሮች ከእውነታው የራቁ እና የ30.7 ጊጋ ቶን ካርቦን ዳይኦክሳይድ ክፍተት ያለባቸው መሆናቸው ተጋልጧል።

የበለጸጉ ሀገራት ለአየር ንብረት ፋይናንስ የገቡትን ቃልኪዳኖች ባለማክበራቸው አዳጊ ሀገራት ከባድ የአየር ንብረት ለውጥ ቀውስ ውስጥ ወድቀዋል።

በጉባኤዎቹ ላይ የተገቡ የቃልኪዳኖች ሙሉ በሙሉ ተፈጽመው ቢሆን ዛሬ የከባቢ አየር ሙቀት መጨመር በታቀደለት የ1.5 ዲግሪ ሴንቲ ግሬድ ውስጥ ሊገታ ይችል ነበር። ይሁን እንጂ የፖለቲካ ቁርጠኝነት ማነስ እና የፋይናንስ እጥረት ዓለምን ወደ ከፋ አደጋ እየወሰዳት ይገኛል።

ኢትዮጵያ ለሙቀት አማቂ ጋዞች ልቀት ያላት አስተዋጽኦ 0.04 በመቶ ብቻ ሆኖ ሳለ ለከፍተኛ የአየር ንብረት አደጋዎች ተጋልጣለች።

ያላመነጨችውን የብክለት ዋጋ በከፍተኛ ድርቅ እና የሀብት መራቆት እየከፈለች የምትገኘው ኢትዮጵያ ችግሩን ሌሎችን ከመጠበቅ ይልቅ ወደ ቀጥተኛ እና መሬት ላይ የሚታይ ተግባር ገብታለች።

በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) መሪነት የተጀመረው አረንጓዴ ዐሻራ ንቅናቄ ራሱን የቻለ የውስጥ አቅም ማሳያ እና ለዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ የተሰጠ ተግባራዊ የመፍትሔ ሞዴል ሆኗል።

የውጭ እርዳታን እና የለጋሾች ቃልኪዳን በመጠባበቅ ጊዜ ሳታባክን በአዋጅ ቁጥር 1361/2024 አማካይነት ከውስጥ ገቢ ከ0.5 እስከ 1 በመቶ በየዓመቱ ለዚሁ ፈንድ እንዲመደብ በማድረግ የደን ልማቱን ተቋማዊ አድርጋዋለች። ከ2011 ዓ.ም ጀምሮ በተከናወኑ ዘመቻዎች ከ56 ቢሊዮን በላይ ችግኞች ተተክለዋል።

የደን ሽፋኑ ከ17.2 በመቶ ወደ 24 በመቶ ከፍ ማለቱ፣ ዓመታዊ የአፈር መሸርሸር ከ1.9 ቢሊዮን ቶን ወደ 208 ሚሊዮን ቶን ዝቅ ማለት፣ እንዲሁም ከ2 ሚሊዮን ሄክታር በላይ ደን በአሳታፊ የደን አስተዳደር ሥር መውደቁ የብክለትን መጠን በከፍተኛ ሁኔታ እየቀነሰ መምጣቱን በግልጽ ያሳያል።

ከዚህም ባሻገር ሥራው ወደ ከተሞች በመስፋፋት የተበከሉ ወንዞችን ወደ ሕዝባዊ መናፈሻዎች ተቀይረዋል። የወንዝ ዳር ልማቱ የከተሞችን የአየር ንብረት ውጥረት በማቃለል ረገድ አብነት የሚሆኑ ተፈጥሯዊ መሠረተ ልማቶች ሆነዋል።

ይህ ብሔራዊ ንቅናቄ ለኢትዮጵያ የሰጠው ጥቅም ዘርፈ ብዙ ነው። የምግብ ዋስትናን ከማረጋገጥ አንፃር ከችግኞቹ መካከል ሰፊው ድርሻ የፍራፍሬ እና ሁለገብ ጥቅም ያላቸው ዝርያዎች በመሆቸው፣ የአርሶ አደሩን ማኅበራዊ-ኢኮኖሚያዊ ሕይወት ከመለወጥ ባለፈ መቶ ሺዎች ጊዜያዊ እና ቋሚ የሥራ ዕድሎችን ፈጥሯል።

ይህ የኢትዮጵያ ስኬት ከአፍሪካ አረንጓዴ ግንብ ጋር ሲነጻጸር የጎላ ልዩነት አለው። አህጉራዊው የአረንጓዴ ግንብ ፕሮጀክት ቢሊዮኖች የሚቆጠሩ ዶላር ዓለም አቀፍ ቃልኪዳን ተሰጥቶት በሂደት ላይ ቢሆንም፣ ኢትዮጵያ በራሷ ሕዝባዊ ጉልበት እና ውስጣዊ አቅም ያስመዘገበችው ስኬት ከዚህ ፕሮጀክት ጋር ሲወዳደር የላቀ እና ፈጣን ውጤት ያስመዘገበ ራስ-አቀፍ ሞዴል መሆኑን አሳይቷል።

በስሌት ሲታይ ኢትዮጵያ 130 ሚሊዮን ሕዝቧን በማንቀሳቀስ ያስመዘገበችው ውጤት በነፍስ ወከፍ ሲሰላ ለአንድ ሰው 437 ችግኞችን ይደርሳል። ዛሬ በዓለም ላይ የሚገኙት 8.2 ቢሊዮን ሰዎች በዚሁ ልክ በራሳቸው ተነሳሽነት ቢሠሩ ኖሮ ዓለም አቀፍ ማኅበረሰብ 3.58 ትሪሊዮን ችግኞችን በመትከል የከባቢ አየር ቀውሱን በአጭር ጊዜ ውስጥ ማስታገስ ይችል ነበር።

ከካርቦን ማስወገጃ ቴክኖሎጂዎች አንፃር በፋብሪካዎች ላይ ከሚገጠሙ እና እጅግ ውድ ከሆኑ ማሽኖች ይልቅ ደንን ማስፋፋት በዝቅተኛ ወጪ ከፍተኛውን ካርቦን በምድር ላይ በመምጠጥ የውኃ ምንጮችን እና ብዝኃ ሕይወትን በአንድ ጊዜ የሚታደግ ሁለገብ ተፈጥሯዊ መፍትሔ ይሰጣል።

ኢትዮጵያ 32ኛውን የዓለም የአየር ንብረት ጉባኤ (COP32) ለማስተናገድ በምታደርገው ዝግጅት አረንጓዴ ዐሻራን ከዓለም አቀፍ የካርቦን ገበያ እና ከዲፕሎማሲ ሥራዎች ጋር በማስተሳሰር የላቀ ምዕራፍ ላይ ደርሳለች።

ዓለም ከማይፈጸም ቃልኪዳን ወጥቶ ወደ ተግባር እንዲገባ የጠየቀው የኢትዮጵያ ድምፅ የዘላቂ ልማት ተምሳሌት በመሆን ዓለምን ለአስተማማኝ የጋራ እጣ ፈንታ እየጋበዘ ይገኛል።

 

በለሚ ታደሰ

 

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: