Search

ከቃል ባለፈ በተግባር የተገነባ የሞራል ልዕልና

ሓሙስ ኅዳር 03, 2019 83

በዓለም አቀፉ የአየር ንብረት ድርድር መድረኮች ላይ ለአሥርተ ዓመታት የበለጸጉ ሀገራት ቃል ሲገቡ፣ ታዳጊ ሀገራት ደግሞ የቃሉን መፈጸም ሲጠባበቁ ቆይተዋል።

በዚህ የማይፈጸም ቃል እና የፖለቲካ ቁርጠኝነት መጥፋት መካከል ግን አንዲት የምሥራቅ አፍሪካ ሀገር ታሪክን በተግባር እየቀየረች ትገኛለች።

ኢትዮጵያ የዓለም አቀፉን ማኅበረሰብ እጅ ሳትጠብቅ በመሪዎቿ ቁርጠኝነት፣ በራሷ አቅም እና በዜጎቿ ጉልበት የአየር ንብረት ለውጥን የሚመክት ግዙፍ ተፈጥሯዊ እና ኢኮኖሚያዊ መሠረት ገንብታለች።

ዛሬ ኢትዮጵያ ወደ ዓለም አቀፉ የድርድር ጠረጴዛ የምትቀርበው እንደ ተረጂ ሳይሆን መፍትሔ ይዛ የምትመጣ፣ ተሞክሮዋን የምታካፍል እና የአፍሪካን ድምፅ በልበ ሙሉነት የምታሰማ አርዓያ ሆና ነው።

በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ሐሳብ አመንጪነት በ2011 ዓ.ም የተጀመረው የአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብር በብዙዎች ዘንድ በቢሊዮን የሚቆጠሩ ችግኞችን የመትከል ዘመቻ ብቻ ተደርጎ ሊታይ ይችላል።

ነገር ግን የመርሐ ግብሩ ጥልቅ ፋይዳ ከቁጥር የተሻገረ ሥነ-ምህዳራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ማኅበራዊ አብዮት ነው።

ለዘመናት በደን መጨፍጨፍ እና በአፈር መሸርሸር ተጎድተው የነበሩ ተራራማ አካባቢዎች እና ተፋሰሶች በአረንጓዴ ዐሻራ አማካኝነት ሕይወት ዘርተዋል።

የአፈር ለምነት መመለሱ የከርሰ ምድር ውኃ እንዲጎለብት እና ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብን ጨምሮ ሌሎች ግዙፍ የውኃ ፕሮጀክቶች በደለል እንዳይሞሉ ትልቅ ጋሻ ሆኗል።

በተባበሩት መንግሥታት የአካባቢ ጥበቃ ፕሮግራም (UNEP) እና በዓለም አቀፉ የደን ምርምር ተቋማት መረጃ እንደሚያሳየው የኢትዮጵያ የደን ሽፋን በጥቂት ዓመታት ውስጥ ከነበረበት 17.2 በመቶ ወደ 23.6 በመቶ ማደጉ ለዚህ ተግባራዊ ስኬት ሕያው ምስክር ነው።

አረንጓዴ ዐሻራ ለአካባቢ ጥበቃ ብቻ ሳይሆን ለዜጎች ኪስ እና ማዕድ የሚተርፍ ኢኮኖሚያዊ ስሌት አለው።

ባለፉት ስምንት ዓመታት ከተተከሉት ከ56 ቢሊዮን በላይ ችግኞች መካከል ከፍተኛውን ድርሻ የሚይዙት እንደ አቮካዶ፣ ማንጎ፣ ሙዝ፣ ፓፓያና ቡና ያሉ ለምግብነትና ለገበያ የሚውሉ ተክሎች ናቸው።

ይህም በሚሊዮን ለሚቆጠሩ አርሶ አደሮች አዲስ የገቢ ምንጭ ከመፍጠሩም በላይ ሀገራችን ከውጭ የምታስገባቸውን የግብርና ምርቶች በሀገር ውስጥ በመተካት የምግብ ሉዓላዊነትን ለማረጋገጥ ወሳኝ ሚና እየተጫወተ ነው።

በተጨማሪም በችግኝ ማፍላት፣ በመትከል እና በመንከባከብ ሂደት ውስጥ ለመቶ ሺዎች ወጣቶች እና ሴቶች ቋሚና ጊዜያዊ የሥራ ዕድል ተፈጥሯል።

በ2018 ዓ.ም በተከናወነው አንድ ጀምበር የችግኝ ተከላ መርሐ ግብር 805.3 ሚሊዮን ችግኞች በመላው ሀገር በመትከል የዓለም ክብረ ወሰንን የሰበረው የኢትዮጵያውያን ርብርብ፣ የጋራ ሀገራዊ ፕሮጀክት ምን ያህል ሕዝብን አንድ ማድረግ እንደሚችል አሳይቷል።

አረንጓዴ ዐሻራ በልጆች እና በወጣቶች አዕምሮ ውስጥ ተፈጥሮን የመንከባከብ ባህልን በመቅረጽ፣ ለቀጣዩ ትውልድ የበለጸገችና አረንጓዴ ሀገር የማስረከብ ታሪካዊ ኃላፊነትን አስርጿል።

በዓለም አቀፍ ዲፕሎማሲ ውስጥ አንድ ሀገር የሚኖራት ተሰሚነት የሚለካው በኢኮኖሚዋ ግዝፈት ወይም በወታደራዊ አቅሟ ብቻ አይደለም፡፡ የምትናገረውን በተግባር በመኖሯ በምታገኘው ሞራላዊ ልዕልና ትልቁን ድርሻ ይይዛል።

ኢትዮጵያ ለዓለም አቀፉ የካርቦን ልቀት የምታበረክተው ድርሻ ከ0.04 በመቶ ያነሰ ቢሆንም፣ የአየር ንብረት ለውጥ በሚያስከትለው ድርቅና ጎርፍ ግን ግንባር ቀደም ተጠቂ ነች።

ሆኖም ኢትዮጵያ የበለጸጉ ሀገራት "የአየር ንብረት ፋይናንስ እስኪለቁልን" ብላ እጇን አጣጥፋ አልተቀመጠችም።

ከ90 በመቶ በላይ የኤሌክትሪክ ኃይሏን ከታዳሽ ምንጮች በማመንጨት የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎችን ወደ ሀገር ውስጥ በስፋት በማስገባትና ነዳጅ የሚጠቀሙ መኪኖችን በመገደብ በዓለም አቀፍ ደረጃ ፈር ቀዳጅ እርምጃ ወስዳለች።

ይህ "በራስ አቅም መጀመር" የተሰኘው የኢትዮጵያ መርሕ፣ በዓለም አቀፉ የድርድር ጠረጴዛ ላይ የማይናወጥ ሞራላዊ ልዕልናን አጎናጽፏታል።

የበለጸጉ ሀገራት መሪዎች ኢትዮጵያን በሚያዩበት ጊዜ የሚመለከቱት እርዳታ ጠያቂ ሳይሆን፣ የራሷን የቤት ሥራ በብቃት የሠራች እና ሌሎችም ቃላቸውን እንዲያከብሩ የመጠየቅ ሙሉ መብት ያላትን ሀገር ነው።

የተባበሩት መንግሥታት የአየር ንብረት ለውጥ ጉባኤ (COP) ዓለም ስለ ሕልውናው የሚመክርበት ትልቁ መድረክ ነው።

ኢትዮጵያ በቀጣይ ለሚካሄደው 32ኛ ጉባኤ (COP32) የምታደርገው ዝግጅት የሀገር ውስጥ የአረንጓዴ ልማት ስኬቶቿን ወደ ዓለም አቀፍ የዲፕሎማሲ ካፒታል የምትቀይርበት ወሳኝ ምዕራፍ ነው።

በኮፕ32 መድረክ ኢትዮጵያ ለዓለም የምታቀርበው ንድፈ ሐሳብን ሳይሆን በመሬት ላይ የተረጋገጠ ተሞክሮዋን ነው።

ኮፕ32 ኢትዮጵያ በአረንጓዴ ኢኮኖሚ ግንባታ የጀመረችውን ጉዞ የሚያፋጥኑ ዓለም አቀፍ ኢንቨስትመንቶችን እና አጋርነቶችን የምትስብበት ስትራቴጂካዊ መድረክ ነው።

 

በአድማሱ አራጋው

 

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: