Search

በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ወላይታ ዞን የበጋ መስኖ ስንዴ ልማት በይፋ ተጀመረ

ሓሙስ ኅዳር 03, 2019 101

በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል በወላይታ ዞን በድጉና ፋንጎ ወረዳ የዘንድሮ ዓመት የበጋ መስኖ ስንዴ ማስጀመሪያ መርሐ ግብር ተካሂዷል።

በክልሉ በበጋ መስኖ 186 ሺህ ሄክታር ማሳ ለማልማት የታቀደ ሲሆን፣ ከዚህ ውስጥ 8 ሺህ  ሄክታሩ በበጋ ስንዴ እንደሚሸፈን ተገልጿል።

የክልሉ ግብርና ቢሮ ኃላፊ ካርታ ካስኬ (ዶ/ር) በወቅቱ እንደገለጹት፣ የግብርና ሥራዎችን በማዘመን እና የመሬት ፀጋዎችን በአግባቡ በመጠቀም ዘርፉ ለሀገር ብልፅግና አዎንታዊ አስተዋጽኦ እንዲያበረክት በትኩረት እየተሠራ ነው።

እያንዳንዱ አካባቢ የሚገኙ አቅሞችን ወደ ምርት በመቀየር ሀገራችንን የብልፅግና ተምሳሌት ማድረግ እንደሚቻልም አፅንኦት ሰጥተዋል።

የወላይታ ዞን ዋና አስተዳዳሪ ረ/ፕሮፌሰር ሳሙኤል ተሰማ በበኩላቸው፣ መንግሥት ለግብርና ዘርፍ የሰጠውን ከፍተኛ ትኩረት በመጠቀም ምርትና ምርታማነትን ማሳደግ እንደሚያስፈልግ ጠቁመዋል።

ለዚህም ግብርናን ማዘመን፣ ቴክኖሎጂን መጠቀም እና ያሉትን ምቹ ዕድሎች ሁሉ በአግባቡ መተግበር እንደሚገባ አስገንዝበዋል።

በክልሉ ነባር ባህላዊ አሠራሮችን በማሻሻል፣ የሰው ኃይልን እና መካናይዜሽን በአግባቡ በመጠቀም የምግብ ሉዓላዊነትን ለማረጋገጥ ሰፊ ርብርብ እየተደረገ ይገኛል።

 

በትዕግስቱ  ቡቼ

 

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: