የኢትዮጵያ ብርቱ አዕምሮዎችንና ሥራ ፈጣሪዎችን አቅም በመገንባት ሀገራዊ ተጽዕኖ እያመጣ የሚገኘው የ"ነጋድራስ" የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የሥራ ፈጠራ ውድድር አምስተኛ ምዕራፍ በዛሬው ዕለት ፍጻሜውን ያገኛል።
ውድድሩ በኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን እና በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ትብብር የሚካሄድ ሲሆን፣ ወጣቶች ከሥራ ጠባቂነት ወጥተው የየሥራ ባለቤቶች እንዲሆኑ ትልቅ በር የከፈተ ነው።
ለአምስተኛው ምዕራፍ ፍጻሜ የበቁት አምስቱ ተወዳዳሪዎች ለዚህ ደረጃ የደረሱት ሀገራዊ ችግሮችን የሚፈቱ አዳዲስ የፈጠራ ሥራዎችን በማቅረብ ነው። ከእነዚህም መካከል ለተጠበሱ ምግቦች የሚውለውን ዘይት ጥራት የሚጠብቅና ጉዳቱን የሚቀንስ "ኸርብ ጋርድ" (Herb Guard) የተሰኘው ፈጠራ አንዱ ነው።
ሌላኛው ደግሞ በባዮሎጂ እና በዘረመል ምርምር ላይ ተመስርቶ የተዘጋጀ “ቶራ” የተሰኘ በፕሮቲን የበለጸገ ምግብ ሲሆን፣ ይህ ፈጠራ አኩሪ አተርን እንደ ዋና ጥሬ እቃ በመጠቀም በተፈጥሯዊ መንገድ በማቀነባበር በውስጡ ያለውን ካርቦሃይድሬት፣ ፕሮቲን እና ጠቃሚ ፋቶች በማበልጸግ እስከ 48 ግራም ፕሮቲን ማግኘት የሚያስችል ነው።
የንፁህ ወሃ ችግርን ለመቅረፍ "ንጹህ ውሃ ለሁሉም" በሚል መሪ ቃል፣ በዘመናዊ የማቀዝቀዣ ሥርዓትና የውሃ ማጣሪያ ቴክኖሎጂ በከተማ አካባቢዎች ንጹህና የተጣራ ውሃን ተደራሽ የሚያደርግ ፈጠራም ለፍጻሜ ቀርቧል።
በጤናው ዘርፍም ሁለት ታላላቅ ፈጠራዎች ለፍጻሜው የደረሱ ሲሆን፣ አንደኛው በሆስፒታሎች ያለውን የኦክስጅን አቅርቦት ችግር የሚቀርፍ ተንቀሳቃሽ የኦክስጅን መሙያ ማሽን ነው።
አነስተኛ ኤሌክትሪክ የሚጠቀመውና የኦክስጅን ኮንሰንትሬተሮችን እንደ መለዋወጫ የሚገለገለው ይህ ማሽን፣ ለኢንዱስትሪዎችና ለጤና ተቋማት በቦታው እየተንቀሳቀሰ ኦክስጅን ከመሙላቱ ባሻገር በድንገተኛ አደጋ ጊዜ ለታካሚዎች ቀጥተኛ አገልግሎት በመስጠት በውድ ዋጋ ከውጭ የሚገዙ የኦክስጅን ፕላንቶችን ይተካል።
ሁለተኛው ደግሞ በገጠር ያሉ ታካሚዎችን በፋርማሲዎች በኩል ከከተማ ሐኪሞች ጋር የሚያገናኘው "ጤና ፈርስት ፕላስ" የተሰኘ የቴሌሜዲሲን መድረክ ነው።
በኢትዮጵያ ስመጥር የንግድ እና ሥራ ፈጠራ አንቱታን ያተረፉት ኢንጂነር ፀደቀ ይሁኔ፣ ኢንጂነር ቢጂአይ ናይከር፣ አቶ ፍፁም ንጉሤ እና ወ/ሮ ፍቅርተ ጋሻው ጥብቅ ፍተሻና ሙያዊ ምዘና የሚመሩበት ይህ የፍጻሜ ውድድር፣ በሀገራችን የሥራ ፈጠራ ታሪክ ውስጥ ትልቅ ምዕራፍ ነው።
በዛሬው ዕለት የሚካሄደው የምዕራፍ 5 የፍፃሜ ውድድር አሸናፊዎቹ የ2 ሚሊየን ብር ሽልማት እና የ50 ሚሊየን ብር የሥራ ብድር ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ይመቻችላቸዋል።
ውድድሩ ከቀኑ 9 ሰዓት ጀምሮ በኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን በቀጥታ ይተላለፋል።
በልዩ እሸቱ
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: