ግብርና የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ የጀርባ አጥንት በመሆኑ የምግብ ዋስትናን ከማረጋገጥ ባለፈ ለኢንዱስትሪው ግብዓት በማቅረብ እና የውጭ ምንዛሪ በማስገኘት ረገድ ያለው ድርሻ የማይተካ ነው።
ይህንን ዘርፍ በዘላቂነት ለማዘመን እና ምርታማነትን በከፍተኛ ደረጃ ለማሳደግ ለዓመታት ትልቅ ተግዳሮት ሆኖ የቆየው የአፈር ማዳበሪያ አቅርቦት እጥረት ነው።
ኢትዮጵያ ይህንን መሠረታዊ ችግር ከስሩ ለመቅረፍ ከዳንጎቴ ግሩፕ ጋር በመሆን ከባለፈው ዓመት ነሐሴ ወር ጀምሮ በዓመት 3 ሚሊዮን ሜትሪክ ቶን የዩሪያ ማዳበሪያ የማምረት አቅም ያለውን የጎዴ ማዳበሪያ ፋብሪካ መገንባት ጀምራለች፡፡
ይህም የኢትዮጵያን የግብርና ትራንስፎርሜሽን እና በኢኮኖሚ ራስን የመቻል ጉዞ ወደ አዲስ ምዕራፍ የሚያሸጋግር ስትራቴጂያዊ ኢንቨስትመንት ነው።
አንድ ሀገር በምግብ ራሷን ችላ ሉዓላዊነቷን ማረጋገጥ የምትችለው ለአርሶ አደሩ የሚያስፈልጉ የግብርና ግብዓቶችን በወቅቱ፣ በበቂ መጠን እና በተመጣጣኝ ዋጋ ማቅረብ ስትችል ብቻ ነው።
ይህ ግዙፍ ፋብሪካ ሲጠናቀቅ በሚሊዮን የሚቆጠሩ አርሶ አደሮችን ተጠቃሚ በማድረግ በዓለም ገበያ ዋጋ መዋዠቅ እና በትራንስፖርት መዘግየት ሳቢያ የሚደርስባቸውን የግብዓት እጥረት ያስቀራል።
ማዳበሪያን በወቅቱ ማግኘቱ የሰብል ምርታማነትን በእጥፍ ለማሳደግ የሚያስችል ሲሆን፣ ከዝናብ ጥገኝነት ተላቅቆ በመስኖ እና በክላስተር ለሚካሄደው ሰፊ የግብርና ልማት ከፍተኛ አቅም ይፈጥራል።
ኢትዮጵያ ለዓመታት በቢሊዮን የሚቆጠር የውጭ ምንዛሪ በማውጣት የአፈር ማዳበሪያ ከውጭ ስታስገባ መቆየቷ በውጭ ምንዛሪ ክምችት ላይ ከፍተኛ ጫና ከመፍጠሩም በላይ፣ ዓለም አቀፍ የጂኦ-ፖለቲካል ቀውሶች በተከሰቱ ቁጥር የአቅርቦት ሰንሰለቱ እንዲስተጓጎል አድርጓል።
ፋብሪካው ወደ ሙሉ ምርት ሲገባ የውስጥ ፍላጎትን ሙሉ በሙሉ ከመሸፈን አልፎ ለጎረቤት ሀገራት እና ለቀጣናው ገበያ በመላክ ኢትዮጵያን ከማዳበሪያ አስመጪነት ወደ ላኪነት ያሸጋግራል፤ ይህም ለኢኮኖሚው ከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ ያስገኛል።
የማዳበሪያ ፋብሪካው ፋይዳ በግብርናው ዘርፍ ብቻ የተገደበ ሳይሆን በራሱ ግዙፍ የኬሚካል እና የማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪ በመሆኑ ለኢትዮጵያ አጠቃላይ የኢንዱስትሪ ዕድገት አዲስ ምዕራፍ ይከፍታል።
የተፈጥሮ ጋዝ እና ሌሎች የውስጥ ጥሬ ዕቃዎችን ወደ ተጨማሪ እሴት በመቀየር የኢንዱስትሪ ትሥሥርን የሚያጠናክረው ይህ ፕሮጀክት በግንባታው ሂደት እና ምርት መጀመር ወቅት በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ለዜጎች ቋሚ የሥራ ዕድል ይፈጥራል።
በተጨማሪም አስተማማኝ የግብርና ግብዓት እና የተረጋጋ ኢኮኖሚያዊ ምህዳር በመፍጠር በ'አግሮ-ፕሮሰሲንግ' ዘርፍ ለሚሰማሩ የውስጥ እና የውጭ ባለሀብቶች ትልቅ መነሳሳትን ይፈጥራል።
በዓመት 3 ሚሊዮን ሜትሪክ ቶን ዩሪያ የማምረት አቅም ያለው ፋብሪካ በመሠረተ ልማት ብቻ የተወሰነ ሳይሆን የኢትዮጵያ የሉዓላዊነት እና የብልጽግና መሠረት በመሆን የውጭ ጥገኝነትን በመቀነስ፣ አርሶ አደሩን በማብቃት፣ ኢንዱስትሪውን በማነቃቃት እና ሰፊ የሥራ ዕድል በመፍጠር የኢኮኖሚ ራስን የመቻል ጉዞን እውን የሚያደርግ ታሪካዊ ኢንቨስትመንት ነው።
በአድማሱ አራጋው
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: