Search

የኢትዮጵያ የአረንጓዴ ኢኮኖሚ ኢኒሼቲቭ ሌሎች የዓለም ሀገራት በተሞክሮነት ሊወስዱት የሚገባ ነው፡- ኔቸር ኮንሰልታንሲ

ሓሙስ ኅዳር 10, 2019 174

የኢትዮጵያ የአረንጓዴ ኢኮኖሚ ኢኒሼቲቭ ሌሎች የዓለም ሀገራትም ሊተገብሩት እንደሚገባ  ኔቸር ኮንሰልታንሲ የተሰኘው የአካባቢ ጥበቃ ድርጅት ዓለም አቀፍ ማኔጂንግ ዳይሬክተር ክሌር ሻክያ ገለጹ።

31ኛው የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የአየር ንብረት ለውጥ ጉባኤ (COP31) በቱርኪዬ አንታሊያ መካሄዱን ቀጥሏል።

ክሌር ሻክያ ኢትዮጵያ በቀጣዩ ዓመት ዓለም አቀፉን የአየር ንብረት ጉባኤ (COP32) ለማስተናገድ መመረጧ እጅግ አስደሳች መሆኑን ገልጸው፣ መንግሥት ለአየር ንብረት ለውጥ መከላከል ከሰጠው ትኩረት አንጻር በጉባኤው ላይ ትልቅ ስኬት ታስመዘግባለች ብለው እንደሚያምኑ ተናግረዋል።

የዓለም አቀፉ ማኅበረሰብም ወደ ሰው ዘር መገኛ ወደ ሆነችው ኢትዮጵያ በመመለስ ጉባኤውን ለመታደም በጉጉት እንደሚጠብቅም አመላክተዋል።

ኢትዮጵያ እየተገበረችው ባለው የአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብር የአየር ንብረት ለውጥ ተጽዕኖዎችን ለመቋቋም እና ተጨማሪ ካርቦን ለማከማቸት ደኖችን፣ ውኃንና ተፈጥሯዊ ሥርዓቶችን መልሶ እንዲያገግሙ ማድረግ ወሳኝ መሆኑን አስገንዝበዋል።

በዚህ ረገድ ኢትዮጵያ እያሳየች ያለችው የመሪነት ሚና የሚደነቅ መሆኑን አንስተው፣ በአየር ንብረት ለውጥ መላመድ አጀንዳ ላይ ግንባር ቀደም ተሟጋች መሆኗንንም ጠቁመዋል።

በኢትዮጵያ በሚካሄደው COP32 ጉባኤ የአየር ንብረት ለውጥ መላመድ ድጋፍን በሦስት እጥፍ የማሳደግ ጉዳይ እውን ሊሆን እንደሚችል ያላቸውን እምነት መግለጻቸውን ኢዜአ ዘግቧል።

አፍሪካ በፈጣን የከተሜነት ሽግግር ላይ በምትገኝበት በዚህ ወቅት፣ ኢትዮጵያ ዝቅተኛ የካርቦን ልቀት ባለው የልማት አካሄድ ዜጎች የምግብ ዋስትና እና ጥሩ መኖሪያ ቤት የሚያገኙበትን የአረንጓዴ ከተሜነት አጀንዳ በተግባር እያሳየች መሆኗን አድንቀዋል።

ኢትዮጵያ የጀመረችው ለአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር አረንጓዴ ኢኮኖሚ ኢኒሼቲቭ እና የልማት ልምዷ ለሌሎች የዓለም ሀገራትም በአርዓያነት ሊተገበር የሚገባው መሆኑን ማኔጂንግ ዳይሬክተሯ ገልጸዋል።

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: