በአማራ ክልል የደረሰ የስንዴ ሰብል እየጣለ ባለው ወቅቱን ያልጠበቀ ዝናብ እንዳይበላሽ በኮምባይነር በመታገዝ እየተሰበሰበ መሆኑን የክልሉ ግብርና ቢሮ ገለጸ።
የቢሮው የድኅረ ምርት ቴክኖሎጂ ባለሙያ አቶ ምትኩ መላኩ እንደገለጹት፣ በ2018/19 የመኸር ወቅት በክልሉ ከ1 ሚሊዮን 80 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት በስንዴ ሰብል ለምቷል።
እስካሁን በተደረገ እንቅስቃሴም በ86 ሺህ 300 ሄክታር ላይ የደረሰ ስንዴ የተሰበሰበ ሲሆን፣ ከዚህ ውስጥ 22 ሺህ 400 ሄክታሩ በኮምባይነር ታግዞ መሰብሰቡን እና ከ1 ነጥብ 1 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት መገኘቱን አመልክተዋል።
ሰብሉ ወቅቱን ባልጠበቀ ዝናብ እንዳይበላሽ ከ90 የሚበልጡ የሰብል ማጨጃና መውቂያ ኮምባይነሮች በምሥራቅና ምዕራብ ጎጃም ዞኖች አገልግሎት እንዲሰጡ እየተደረገ ነው ብለዋል።
በሰው ጉልበትና በኮምባይነር ታግዞ የደረሰን የስንዴ ሰብል ከብክነት በጸዳ መልኩ በመሰብሰብ የተሻለ ምርት ይገኛል ተብሎ እየተሠራ እንደሆነ መግለጻቸውን ኢዜአ ዘግቧል።
በዘንድሮው የመኸር ወቅት በክልሉ አጠቃላይ በተለያዩ ሰብሎች ከለማው ከ5 ነጥብ 6 ሚሊዮን ሄክታር በላይ መሬት እስካሁን በ2 ነጥብ 2 ሚሊዮን ሄክታር ላይ የደረሰ ሰብል መሰብሰቡ ተገልጿል።
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: