Search

ኢትዮጵያ ለሌሎች የአፍሪካ ሀገራት ጭምር ትዕምርት የሚሆን ተምሳሌታዊ የጤና ሥርዓት እየገነባች ነው፡- የፓን-አፍሪካ የቀዶ ሕክምና ፎረም ተሳታፊዎ

ቅዳሜ ኅዳር 12, 2019 125

የኢትዮጵያ ውጤታማ የጤና ሥርዓት ግንባታ የጤና አገልግሎት ጥራትና ተደራሽነት በማስፋት ለሌሎች የአፍሪካ ሀገራት ተምሳሌት መሆኑን የዓለም አቀፍ የጤና ተቋማት ኃላፊዎች ገለጹ።

የመደመር እሳቤ የሰውን ልጅ ሁለንተናዊ ብልጽግና መሠረት ያደረገ ሲሆን፣ ጤናማና አምራች ዜጋን መፍጠር የዚህ ርዕይ ዋነኛ ምሰሶ ነው።

የ4ኛው የፓን-አፍሪካ የቀዶ ሕክምና ፎረም ተሳታፊዎች እንደገለጹት፣ ኢትዮጵያ ለሌሎች የአፍሪካ ሀገራት ጭምር ትዕምርት የሚሆን ተምሳሌታዊ የጤና ሥርዓት እየገነባች ነው።

የኦፕሬሽን ስማይል የፖሊሲና አድቮኬሲ ኃላፊ ዶክተር ሩበን አያላ ድርጅታቸው ኢትዮጵያን ጨምሮ ባለፉት 45 ዓመታት በ38 ሀገራት የጤና ሥርዓትን ለማሻሻል በትብብር እየሠራ መሆኑን ገልጸዋል።

በኢትዮጵያም በአዲስ አበባ፣ ጅማ እና ሐዋሳ ከሚገኙ የጤና ተቋማት ጋር በመተባበር በቀዶ ሕክምና ሙያተኛ ስልጠና እና በተቋማት አቅም ግንባታ በትብብር እየሠሩ መሆኑን ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ የጤና ሥርዓት ተደራሽነትና የሰው ሃብት ልማት ቁርጠኛ አመራርም ከራስ የተሻገረ አህጉራዊና ዓለም አቀፋዊ ተሞክሮ መሆኑን አንስተዋል።

በቀዶ ሕክምና አገልግሎት ተደራሽነትም በዓለም አቀፍ መድረኮች ጭምር የዓለም ጤና ድርጅትና ሀገራት በጤና ዘርፍ መዋዕለ ንዋያቸውን እንዲያሰፉ ጥሪ እያቀረበች መሆኑን አስረድተዋል።

በኢትዮጵያ የቀዶ ሕክምና፣ የፅንስና ማህፀን እና የማደንዘዣ ባለሙያዎች ቁጥር በ100 ሺህ ሕዝብ ከአንድ በታች ነበር፤ አሁን ላይ ከአምስት በላይ ማድረሷ ትልቅ ስኬት ነው ብለዋል።

የፓን አፍሪካ የቀዶ ሕክምና፣ የፅንስና ማህፀን እና የማደንዘዣ ሕክምና ፎረም አስፈጻሚ ኮሚቴ አባል ፕሮፌሰር ኢማኑኤል አሜ በበኩላቸው፣ ኢትዮጵያ ፎረሙን ለተከታታይ ሁለት ዓመታት በማስተናገድ ለአህጉሪቷ የጤና ሥርዓት መሻሻል ቁልፍ ሚና እየተወጣች ነው ብለዋል።

ኢትዮጵያ የሕክምና መሳሪያን በሀገር ውስጥ ማምረትን ጨምሮ ብሔራዊ የቀዶ ሕክምና ዕቅድ ቀድማ ማዘጋጀቷ ሌሎች ሀገራት ተሞክሮ እንዲቀስሙ እያደረገ መሆኑን ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ የጤና ሉዓላዊነትን የማረጋገጥ ውጤታማ ጉዞም ለአብዛኞቹ የአፍሪካ ሀገራት የሕክምና መሳሪያ የውጭ ጥገኝነትና ከፍተኛ የገንዘብ ወጪ ሁነኛ ትምህርት እያስተላለፈ እንደሚገኝ አስረድተዋል።

በአፍሪካ የሕጻናትን የከንፈርና የላንቃ ስንጥቃት የተሟላ ሕክምና ለማስገኘት እየሠራን ነው ያሉት ደግሞ የስማይል ትሬን የኢምፓክት ዋና ኃላፊና የሕብረተሰብ ጤና ባለሙያ ዶክተር ማንዳና አራቢ ናቸው።

በኢትዮጵያም ከጤና ዘርፍ አጋሮች ጋር በመተባበር መሰል ችግር ያለባቸው ሕጻናት ደኅንነቱ የተጠበቀ ቀዶ ሕክምና በማስገኘት ለዘርፉ ሙያተኞች ጭምር የአቅም ግንባታ ስልጠና እየተሰጠ መሆኑን ገልጸዋል።

ኢትዮጵያ የመጀመሪያ ደረጃ ጤና አገልግሎትንና የሕብረተሰብ ጤናን የተቀናጀ አመራር ለሌሎች የአፍሪካ ሀገራት የጤና አገልግሎት ላይ በጎ ተጽዕኖ የሚያሳድር መሆኑን ገልጸዋል።

የአፍሪካና ዓለም አቀፍ የዲፕሎማሲ ማዕከል መሆኗን በሚያሳይ መልኩ በጤና ዘርፍም የአገልግሎት ፍትሐዊ ተደራሽነት ላይ ያላት ቁርጠኝነት የሚደነቅ ነው ብለዋል።

የመርሲ ሺፕስ የጤና ፖሊሲና ትብብር ዳይሬክተር ብራያን ሃለር በበኩላቸው፣ ኢትዮጵያ ለሌሎች የአፍሪካ ሀገራት ሊከተሉት የሚገባ የጤና ሥርዓት እየገነባች መሆኗን አመልክተዋል።

ድርጅታቸው በምስራቅ አፍሪካ ያለውን ይህን ስኬታማ ተሞክሮ በትኩረት በሚሰራባቸው የአህጉሪቱ አካባቢዎች ለማስፋት እንደሚሠራ መናገራቸውን ኢዜአ ዘግቧል።

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: