Search

5ኛው የአፍሪካ የሕዝብ ጤና ኮንፈረንስ በአዲስ አበባ

ሰኞ ኅዳር 14, 2019 31

ከዛሬ ጀምሮ ለሚቀጥሉት አምስት ቀናት በኢትዮጵያ አስተናጋጅነት የሚካሄደው 5ኛው የአፍሪካ የሕዝብ ጤና ኮንፈረንስ (CPHIA 2026) በአህጉሪቱ የጤና ዘርፍ ልዩ ቦታ የሚኖረው ነው።

ዓለም አቀፍ የጤና ተቋማት መዋቅሮች በተደጋጋሚ በሚፈተኑበት እና የውጭ አቅርቦት ሰንሰለቶች አስተማማኝነት ጥያቄ ውስጥ በገባበት በዚህ ወቅት፣ ኮንፈረንሱ አፍሪካ በውጭ ዕርዳታ እና ጥገኝነት ላይ የተመሠረተ የቆየ አካሄድን በመሻገር በራሷ የፋይናንስ፣ የምርምር፣ የምርት እና የበሽታ መከላከል አቅም ላይ የተመሠረተ የጤና ደኅንነት እንድታረጋግጥ የሚያስችል አዲስ ምዕራፍ ይከፍታል።

የጤና ሉዓላዊነት ማለት ሀገራት የዜጎቻቸውን ጤና ለመጠበቅ እና የሕዝብ ጤና ስጋቶችን ለመቋቋም የሚያስፈልጓቸውን ፖሊሲዎች፣ ፋይናንስ፣ መድኃኒቶች፣ ክትባቶች እና የቴክኖሎጂ መሠረተ ልማቶች በራሳቸው የመወሰንና የማስተዳደር ሙሉ አቅም መገንባት ነው።

ባለፉት ዓመታት የታዩ ዓለም አቀፍ ወረርሽኞች እና የአቅርቦት መስተጓጎሎች አፍሪካ በውጭ አቅርቦት ላይ ያላትን ከፍተኛ ጥገኝነት አጋልጠዋል።

በአህጉሪቱ የመድኃኒት፣ የክትባት እና የሕክምና መሣሪያዎች ማምረቻ ፋብሪካዎችን ማስፋፋት፣ የጥሬ ዕቃ አቅርቦትን ማቀላጠፍ እና የቁጥጥር ተቋማትን አቅም ማጎልበት የአቅርቦት ዋስትናን በማረጋገጥ ወጪን ይቀንሳል፡፡ ለድንገተኛ ወረርሽኞችም ፈጣን ምላሽ ለመስጠት ያስችላል። ከዚህም ባለፈ ለአህጉሪቱ ኢኮኖሚ የሥራ ዕድል እና የቴክኖሎጂ ሽግግርን ያስገኛል።

በሌላ በኩል በውጭ ዕርዳታ እና ብድር ላይ ብቻ የተመሠረተ የጤና በጀት በቀላሉ ሊናጋ ስለሚችል፣ የሀገር ውስጥ የሀብት ማሰባሰብ ሥርዓቶችን ማጠናከር ወሳኝ ነው።

ይህም ዜጎች በሕክምና ወቅት ከኪሳቸው የሚያወጡትን ቀጥተኛ ወጪ በመቀነስ ወደ ማኅበረሰብ አቀፍ እና ማኅበራዊ የጤና መድን እንዲሁም ወደ ዘላቂ የመንግሥት እና የግል ዘርፍ ኢንቨስትመንት መሸጋገርን ያካትታል።

በተጓዳኝም በአፍሪካ ነባራዊ ሁኔታ ላይ ያተኮሩ ምርምሮችን በአፍሪካውያን ተመራማሪዎች እና ተቋማት መምራት የፖሊሲ እና የሕክምና ውሳኔዎችን ይበልጥ ትክክለኛና ተስማሚ ያደርጋቸዋል።

ዘላቂ የጤና ደኅንነትን ለማረጋገጥ የጤና ሥርዓቱን በሁሉም ረገድ ማዘመን ያስፈልጋል። ዲጂታል የጤና መረጃ ሥርዓቶች፣ የርቀት ሕክምና (Telemedicine) እና ሰው ሠራሽ አስተውሎት (AI) የበሽታዎችን ቅድመ ምርመራ፣ የወረርሽኝ ትንበያ፣ የመድኃኒት ስርጭት ክትትልና የጤና ባለሙያዎችን የሥራ ቅልጥፍና በከፍተኛ ደረጃ ያሳድጋሉ፡፡ በተለይም መሠረተ ልማቶች በማይደርሱባቸው አካባቢዎች ያለውን የአገልግሎት ክፍተት ለመሙላት ወሳኝ ናቸው።

ከዚህ ጎን ለጎን ጠንካራ የቅድመ ማስጠንቀቂያ ሥርዓት፣ የላቦራቶሪ አውታር፣ የሰለጠነ የድንገተኛ ምላሽ ሠራዊት እና ፈጣን የመረጃ ልውውጥ ድንገተኛ ስጋቶች ወደ ሰፊ ቀውስ እንዳይለወጡ ይከላከላሉ።

በማኅበረሰብ ደረጃ ያሉ በሽታዎችን ቀድሞ ለመቆጣጠር እና ሁሉን አቀፍ የጤና ሽፋንን ለማረጋገጥ ደግሞ የጤና ጣቢያዎችን እና የጤና ኬላዎችን ማጠናከር እንዲሁም የመከላከል ሥራዎችን ማስፋፋት መሠረታዊ ጉዳይ ነው።

ኢትዮጵያ የአፍሪካ ሕብረት መቀመጫና የአህጉራዊ ዲፕሎማሲ ማዕከል እንደመሆኗ CPHIA 2026ን ማስተናገዷ በአፍሪካ የጤና ደኅንነት ግንባታ ውስጥ ያላትን የመሪነትና የትብብር ሚና ይበልጥ ያጎላል።

በቀዳሚ ጤና አገልግሎት መስፋፋት፣ በማኅበረሰብ ጤና ሥራዎች እና በሕዝብ ጤና ሥርዓት ግንባታ ያዳበረቻቸውን ልምዶችም ለሌሎች የአፍሪካ ሀገራት ጠቃሚ ተሞክሮ ይሆናሉ።

ይህ ጉባኤ አፍሪካ የጤና ሉዓላዊነቷን የምታረጋግጥበት፣ በራሷ አቅም የምትተማመንበት እና የጋራ የጤና ዕጣ ፈንታዋን በባለቤትነት የምትመራበትን ምዕራፍ የሚያበስር ወሳኝ መድረክ ነው።

ኢትዮጵያ የጤና ዲፕሎማሲዋን እና የትብብር መንፈሷን በማጎልበት የምታበረክተው አስተዋፅኦ፣ ከአፍሪካ ሕብረትና ከአፍሪካ የበሽታዎች መቆጣጠሪያና መከላከያ ማዕከል (Africa CDC) ጋር የሚኖረው ቅንጅት እንዲሁም ከኮንፈረንሱ የሚመነጩ ተግባራዊ እርምጃዎች አህጉሪቱን ወደ ጠንካራ የጤና ደኅንነትና ዘላቂ ልማት እንደሚያሸጋግሩ ይታመናል።

በአድማሱ አራጋው

 

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: