የመደመር መንግሥት እቅዶችን ወደ ተግባር በመቀየር የሕዝብን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ በትጋት እንደሚሠሩ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ገልጸዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የመደመር መንግሥት የ2019 ዓ.ም የሥራ አቅጣጫና ቀጣይ ዕቅዶችን በተመለከተ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መደበኛ ጉባኤ ከምክር ቤቱ አባላት ለተነሱ ጥያቄዎች ምላሽና ማብራሪያ ሰጥተዋል።
የምክር ቤቱ አባላት ማብራሪያውን ተከትሎ በሰጡት አስተያየት፣ መንግሥት ያቀረባቸውን እቅዶች በተግባር ለማሳካት፣ የተጀመሩ ሥራዎችን ለማስቀጠልና ለዜጎች የኢኮኖሚ ተጠቃሚነት እና ለሀገር ዕድገት በትኩረት እንደሚሠሩ ገልጸዋል።
የምክር ቤቱ አባል ፈትሂ ማህዲ (ዶ/ር) የጠቅላይ ሚኒስትሩ ማብራሪያ የመንግሥትን ቀጣይ የሥራ አቅጣጫ በግልጽ ያሳየ መሆኑን ጠቁመው፣ በተለይም በዜጎች ሕይወት ላይ ተጨባጭ ለውጥ ሊያመጡና የኑሮ ውድነትን ለመቀነስ የሚያግዙ እንደ ተፈጥሮ ጋዝ፣ የማዳበሪያ ፋብሪካ እና የቤት ልማት ያሉ በርካታ ትላልቅና ዘርፈ ብዙ ሀገራዊ ፕሮጀክቶች መታቀዳቸው የሚበረታታ ተግባር መሆኑን አመልክተዋል፡፡
የመደመር መንግሥት ያቀረባቸውን እቅዶች በተግባር ለማሳካት፣ የተጀመሩ የልማት ሥራዎችን ለማስቀጠል፣ የሕዝብን ተጠቃሚነት ለማሳደግ፣ ሌብነትንና ብልሹ አሠራሮችን በመታገል የኢትዮጵያን የብልፅግና ጉዞ ለማረጋገጥ በትኩረት እንደሚሠሩ ተናግረዋል።
ሌላኛዋ የምክር ቤት አባል ወ/ሮ ስመኝ ሳህሉ በበኩላቸው፣ የመደመር መንግሥት የሀገራችንን ዕድገት ለማሳካት የሚያስችል ስትራቴጂ የግንዛቤ ማስጨባጫ ሥራዎችንና ስልጠናዎችን በመስጠት ወደ ተግባር መግባቱን ገልጸዋል፡፡
በተለይም በክትትል እና ቁጥጥር ሥራዎች የአፈፃፀም ችግሮችን፣ የአመራር እና የኪራይ ሰብሳቢነት ማነቆዎችን በመለየትና በየደረጃው በመፍታት ሕብረተሰቡ የተሻለ ተጠቃሚ እንዲሆን ለማስቻል የመሥራትና የመከታተል ከፍተኛ ኃላፊነት እንዳለባቸው ጠቁመዋል፡፡
በመንግሥት ታቅደው የሚከናወኑ ሥራዎች ውጤታማ እንዲሆኑና የሕዝብ የልማት ጥያቄዎች ምላሽ እንዲያገኙ በቁርጠኝነት እንደሚሠሩ ሌሎች የምክር ቤቱ አባላትም አረጋግጠዋል።
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: