በረጅም ዘመናት ልህቀትና በአፍሪካ ፈር ቀዳጅነት የታነጸው የኢትዮጵያ የአቪዬሽን ታሪክ ከአህጉራዊ ትስስር አንቀሳቃሽነት ባለፈ ለሀገሪቱ ዓለም አቀፍ ዲፕሎማሲያዊ ቁመና ጠንካራ መሠረት ሆኖ እያገለገለ ይገኛል።
ይህንኑ ታሪካዊ አቅም ወደ ተጨባጭ ውሳኔ ሰጪነት በመቀየር ኢትዮጵያ በካናዳ ሞንትሪያል በተካሄደው 43ኛው የዓለም አቀፉ የሲቪል አቪዬሽን ድርጅት (ICAO) ጠቅላላ ጉባዔ ልዩ ስብሰባ ላይ 133 ድምፅ በማግኘት የድርጅቱ ምክር ቤት አባል ሆናለች። የምክር ቤቱ መቀመጫዎች ከ36 ወደ 40 ከፍ ሲሉ ከተጨመሩት አራት አዳዲስ ወንበሮች አንዱን ማግኘቷ ሀገሪቱ በዓለም አቀፍ የአቪዬሽን ፖሊሲና ደንብ አወጣጥ ሂደት ውስጥ ቀጥተኛ የውሳኔ ሰጪነት ሚና እንዲኖራት ያስችላታል።
ይህ አባልነት የአፍሪካን የጋራ ጥቅምና አንድነት ለማስከበር፣ የደቡብ-ለደቡብ ትብብርን በተግባር ለማጠናከር እንዲሁም ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ መድረኮች ላይ ያላትን ተሰሚነት በዘላቂነት ለማሳደግ የምታደርገው ቀጣይነት ያለው የዲፕሎማሲ ጥረት ተጨባጭ ውጤት ማሳያ ነው።
የአፍሪካ ኅብረት ኢትዮጵያን የመላው አህጉሪቱ ብቸኛ ዕጩ አድርጎ በመሰየሙናበአፍሪካ የሲቪል አቪዬሽን ኮሚሽን (AFCAC) በመደገፉ የተገኘው ይህ አህጉራዊ ቅቡልነት በብሪክስ የትብብር ማህቀፍ ተጨማሪ ዓለምአቀፍ ድጋፍ አግኝቷል።
ኢትዮጵያ ይህንን ውክልና እንደ ሀገር ስኬት ብቻ ሳይሆን የመላው አፍሪካን ጥቅም የማስከበር አህጉራዊ ኃላፊነት አድርጋ ወስዳዋለች፤ በኒው ዴልሂ የተካሄደው 18ኛው የብሪክስ የመሪዎች ጉባዔ ባወጣው የጋራ መግለጫ አንቀጽ 105 ላይ የአፍሪካ ኅብረትን ውሳኔ በመቀበል ለኢትዮጵያ ሙሉ ድጋፉን ማረጋገጡም የሀገሪቱን የዲፕሎማሲ አድማስ ከአፍሪካ ባሻገር ያሰፋ ክስተት ነው።
ይህም የአፍሪካ ኅብረት አህጉራዊ ውክልናን ሲሰጥ ብሪክስ ደግሞ በማደግ ላይ ባሉ ኢኮኖሚዎች ዘንድ ሰፊ ፖለቲካዊ ዕውቅናን በማስገኘት ቀጣናዊ አንድነት እና የደቡብ-ለደቡብ ትብብር በዓለም አቀፍ የትብብር ማህቀፎች ውስጥ እንዴት ተደጋግፈው ውጤት እንደሚያመጡ በግልጽ ያሳያል።
ለኢትዮጵያና ለአፍሪካ አህጉር ያለው ስትራቴጂካዊ ፋይዳ
በዚህ ወሳኝ የለውጥ ወቅት ኢትዮጵያ በዓለም አቀፉ የሲቪል አቪዬሽን ድርጅት (ICAO) ምክር ቤት ውስጥ ያገኘችው መቀመጫ ለሀገሪቱ፣ ለዜጎቿ እና ለመላው አፍሪካ ዘርፈ ብዙ የዲፕሎማሲ፣ የኢኮኖሚና የአሠራር ፋይዳ አለው።
በምክር ቤቱ ውስጥ ውክልና ማግኘቷ የበረራ ደኅንነትና ፀጥታን፣ የአየር ትራፊክ አስተዳደርን፣ የአካባቢ ጥበቃንና የቴክኖሎጂ ፈጠራን የሚመለከቱ ዓለም አቀፍ ደረጃዎችንና መመሪያዎችን (SARPs) በማርቀቅ ሂደት ውስጥ ቀጥተኛ የውሳኔ ሰጪነት ሚና እንዲኖራት ያስችላታል።
በተጨማሪም ይህ አባልነት ኢትዮጵያ ከካርቦን ልቀት ቅነሳ፣ ከካርቦን ማካካሻ እና ከዘላቂ የአቪዬሽን ነዳጆች ጋር የተያያዙ ዓለም አቀፍ ፖሊሲዎችን በመቅረፅ ረገድ ወሳኝ ድርሻ እንድትወጣ ያግዛታል። ይህም አዳዲስ ዓለም አቀፍ ደንቦች ፍትሐዊ እንዲሆኑና በአፍሪካ አየር መንገዶች እንዲሁም በአዳጊ የአቪዬሽን ገበያዎች ላይ ያልተመጣጠነ የወጪ ጫና እንዳይፈጥሩ ለመከላከል ሰፊ ዕድል ይፈጥራል።
የምክር ቤቱ አባልነት ዓለም አቀፍ የአቪዬሽን ዲፕሎማሲን ከሀገራዊ የኢኮኖሚ ሽግግር ጋር በቀጥታ የሚያስተሳስር ስትራቴጂካዊ ዕድል ሲሆን በኢትዮጵያ አየር መንገድ፣ እየተስፋፉ ባሉ ግዙፍ የአውሮፕላን ማረፊያ ፕሮጀክቶች፣ በአየር ትራፊክ አገልግሎቶችና በዓለም አቀፍ ደረጃ በተደራጁ የሥልጠና አካዳሚዎች የተደገፈው የአቪዬሽን ዘርፍ ሀገሪቱን ከዓለም ጋር የሚያገናኝ ዋነኛ ምሰሶ ሆኖ ያገለግላል።
በዓለም አቀፍ ደንብና አሠራር በቀጥታ መሳተፍ ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ በኢትዮጵያ የቁጥጥር ሥርዓት ላይ ያለውን እምነት በማጠናከር የአውሮፕላን ግዥ ፋይናንስና የኢንሹራንስ ወጪዎችን ይቀንሳል። ይህም አዲስ አበባ የአፍሪካ ተቀዳሚ የመንገደኞችና የጭነት መናኸሪያ እንድትሆን በማገዝ የወጪ ንግድን፣ የቱሪዝምና የውጭ ኢንቨስትመንት ፍሰትን እንዲሁም ለባለሙያዎች የሚፈጠሩ የሥራ ዕድሎችን ያሳድጋል።
በአህጉር ደረጃ የኢትዮጵያ ውክልና የአፍሪካን የጋራ የአቪዬሽን ፍላጎት ይበልጥ አካታች በሆነ ዓለም አቀፍ ሥርዓት ውስጥ ለማራመድ ጠንካራ መድረክ ከመፍጠሩም ባሻገር ኢትዮጵያ ከአፍሪካ ኅብረት እና ከአፍሪካ የሲቪል አቪዬሽን ኮሚሽን (AFCAC) ጋር በቅርበት በመሥራት የአፍሪካ የተቀናጀ የአየር ትራንስፖርት ገበያን (SAATM) የሚያፋጥኑ የአየር ክልል አስተዳደርን የሚያቀናጁ፣ የአህጉሪቱን የእርስ በርስ ትስስር የሚያሰፉ እና የአባል ሀገራትን የቴክኒክና የደኅንነት አቅም የሚያጎለብቱ ፖሊሲዎችን በግንባር ቀደምትነት እንድታራምድ ያስችላታል።
ይህ ዓለም አቀፍ ውክልና የከፈታቸውን ዕድሎች ወደ ተጨባጭ ውጤት ለመቀየር የአቪዬሽን ተቋማት፣ የግሉ ዘርፍና ወጣት ባለሙያዎች ዝግጁነት ወሳኝ ድርሻ ያለው ሲሆን የተገኘውን የዲፕሎማሲ አቅም ወደ ዘላቂ ተቋማዊ ብቃት በማሸጋገር የኢትዮጵያን ብልጽግናና የአፍሪካን ዓለም አቀፍ የኢኮኖሚ ትስስር በዘላቂነት ያጠናክራል።
የጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: