ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ኢትዮጵያ ሁሉም የሱዳን ወገኖች ያለምንም ቅድመ ሁኔታ ወደ ውይይት መድረክ እንዲመጡ ይፋዊ የሰላም ጥሪ ማቅረቧን ገልጸዋል።
ኢትዮጵያ ሱዳናውያን በራሳቸው ፍላጎት ዘላቂ ሰላም የሚያመጡበትን ሁሉን አቀፍ የውይይት መድረክ ለማስተናገድና ለማመቻቸት ዝግጁ መሆኗንም አረጋግጠዋል።
የአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን ሊቀመንበር መሐሙድ ዓሊ ዩሱፍ፣ የኢትዮጵያ መንግሥት የሱዳን ባለድርሻ አካላትን የሚያሳትፍ የምክክር መድረክ ለማዘጋጀት ያቀረበውን የሰላም ሀሳብ በአጽንኦት መመልከታቸውን ገልጸዋል።
የሱዳን ባለሥልጣናት በሀሳቡ ዙሪያ የሰጡትን ምላሽና የያዙትን አቋም በቅርበት መከታተላቸውንም አስታውቀዋል።
ሊቀመንበሩ በመግለጫቸው፣ ኢትዮጵያ ያቀረበችው የውይይት ሀሳብ በሱዳን ተፋላሚና ባለድርሻ አካላት መካከል ምክክር እንዲጀመርና እንዲዳብር የሚደረገውን ጥረት በማገዝ ረገድ ትልቅ ፋይዳ እንዳለው ጠቁመው፣ ህብረቱም እውቅና እንደሚሰጠው አመልክተዋል።
የአፍሪካ ህብረት በሱዳን የተከሰተው ግጭት በህብረቱ መመስረቻ ቻርተርና አግባብነት ባላቸው የህብረቱ ሕጎች መሠረት፣ በውይይትና በድርድር ብቻ አካታችና ሰላማዊ እልባት እንዲያገኝ የማይናወጥ ቁርጠኝነት እንዳለው ሊቀመንበሩ አረጋግጠዋል።
የወቅቱ የአፍሪካ ህብረት ሊቀመንበርና የብሩንዲ ፕሬዝዳንት ኤቫሪስቴ ንዳዪሺሚዬ በሱዳን ዘላቂ ሰላም ለማምጣት የሚያደርጉትን ጥረት፣ ኮሚሽኑ ከሁሉም ባለድርሻ አካላት ጋር በቅርበት በመተባበር ለመደገፍ ሙሉ ቁርጠኝነት እንዳለው ሊቀመንበሩ ማስታወቃቸውን ኢዜአ ዘግቧል።
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: