ሠርክ ዝግጁነት የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት መለያ እሴት ሆኗል። ዓለም የደረሰበትን የውትድርና ቴክኖሎጂ፣ የትጥቅ ደረጃና የአመራር ብቃት በመላበስ የጦርነት ሥጋቶችን አስቀድሞ ለመመከት መንግሥት ሰፊ የሪፎርም ሥራዎችን እያከናወነ ይገኛል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የመከላከያ ሠራዊቱን አቅም እና ዝግጁነት አስመልክተው ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ባቀረቡት ማብራሪያ፣ አንድ ጠንካራ ሠራዊት የሚገነባው በጦርነት ወቅት ብቻ ሳይሆን በሰላም ጊዜ ቀን ከሌሊት በሚደረግ ያላሰለሰ ዝግጅት መሆኑን አስገንዝበዋል።
በዚህም መሠረት የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት አራት ዋና ዋና ስትራቴጂካዊ ተልዕኮዎችን አንግቦ እየተገነባ ይገኛል።
የመጀመሪያው ተልዕኮ ዓለም አቀፍ የጂኦፖለቲካ አዝማሚያዎችን እንዲሁም የውስጥ ነባራዊ ሁኔታዎችን አስቀድሞ የመተንተን፣ የማወቅ እና የመለየት አቅም መፍጠር ነው።
ሁለተኛው ተልዕኮ ደግሞ ግጭቶች ሁልጊዜም ቢሆን ከፍተኛ ሰብዓዊ እና ቁሳዊ ኪሳራ የሚያስከትሉ በመሆናቸው፣ ሠራዊቱ በሚገነባው የላቀ ቁመና እና የመከላከል አቅም ሥጋቶችን እና ግጭቶችን ሳይፈጠሩ አስቀድሞ ማስቀረት ነው።
ሦስተኛው ተልዕኮ የጥቃት ሁኔታ ሲያጋጥም መልሶ የማጥቃት እርምጃን ጨምሮ በተሟላ ብቃት በመከላከል የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት እና የግዛት አንድነት ማስከበር ሲሆን፣ አራተኛው እና ወሳኙ ጉዳይ ደግሞ የተገኘን ድል ማዝለቅ ነው።
ከድል በኋላ "አሸንፌያለሁ" በሚል መዘናጋት መቀመጥ የታሪክ ስህተቶች እንዲደገሙ ስለሚያደርግ፣ የተገኘውን ሰላም እና ድል በዘላቂነት ማስቀጠል እንደሚገባ ጠቅላይ ሚኒስትሩ አጽንዖት ሰጥተዋል።
“ያልተወጠረ ቀስት ዒላማውን አይመታም” ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ በሰላም ጊዜ ጠንክሮ ያልሠራ እና በቴክኖሎጂ ያልዘመነ መከላከያ አስፈላጊ በሚሆንበት ወቅት ውጤታማ ሊሆን እንደማይችል ገልጸዋል።
ኢትዮጵያም ይህንኑ መርሕ በመከተል የሰው ኃይሏን በሥልጠና፣ የመከላከያ ኢንዱስትሪዋን ደግሞ በዘመናዊ ቴክኖሎጂ በማዘመን አስተማማኝ የመከላከያ አቅም እየገነባች ትገኛለች።
በዓይናለም ሃድራ
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: